በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 194 ደረሰ
አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 30 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የጤና ሚኒስቴር ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ለ1 ሺህ 861 ሰዎች የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጎ ሶስት ሰዎች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው አስታወቀ።
ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሴቶች ሲሆኑ፥ እድሜያቸው ከ23 እስከ 33 አመት የሆኑ እና የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ናቸው።
ሁለቱ በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ ያላቸው ሲሆኑ፥ አንደኛዋ በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር ያላት ንክኪ እየተጣራ ነው ተብሏል።
በአጠቃላይ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 194 መድረሱንም ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቀው።
በሌላ በኩል ሁለት ሰዎች ከቫይረሱ ያገገሙ ሲሆን፥ ይህም ከቫይረሱ ያገገሙ ሰዎችን ቁጥር 95 አድርሶታል።