በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ 350 በላይ ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉ ተገለፀ
አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 10 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ስራ አቁመው ከነበሩ 400 ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ከ 350 በላይ ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉ የኢትዮጵያ ታምርት ፅህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት አስተባባሪ አቶ አስፋው አበበ ÷ የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም 85 በመቶ እንዲደርስ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
በንቅናቄው በአንድ አመት ብቻ 2 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸውን ገቢ ምርቶች በሀገር ውስጥ ማምረት መቻሉን የገለፁት አስተባባሪው ÷የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ከነበረበት 46 በመቶ አሁን ላይ ከ 53 በመቶ በላይ ማድረስ መቻሉን ተናግረዋል።
የኢንዱስትሪዎችን መሰረታዊ ችግሮች በመፍታት አቅማቸውንም ማሳደግ ይቻል ዘንድ የክላስተር ኮሚቴ መቋቋሙንም አስተባባሪው ጠቁመዋል፡፡
በ10 አመቱ እቅድ ደግሞ በአምራች ኢንዱስትሪው ከ 5 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
በዙፋን ካሳሁን