Fana: At a Speed of Life!

የፌዴራል ፍርድ ቤቶች በከፊል ዝግ ሆነው የሚቆይቡት ጊዜ ተራዘመ

አዲስ አበባ፣ሚያዝያ 30፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የየፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የኮሮና ቫይረስ (COVID 19) ስርጭትን ለመከላከል ቀጣይ የጥንቃቄ እርምጃዎችን መውሰድ በማስፈለጉ ፍርድ ቤቶች በከፊል ዝግ ሆነው የቆዩበትን ጊዜ ለተጨማሪ 22 የስራ ቀናት መራዘሙን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታወቀ።

የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ከመጋቢት 10 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሚያዚያ 30 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ በከፊል ዝግ ሆነው አፋጣኝ የፍርድ ቤት ውሳኔና ትእዛዝ የሚፈልጉ ገዳዮችን በተረኛ ችሎቶች በማስተናገድ አገልግሎት እንዲሰጡ መወሰኑ ይታወቃል።

በዚህ ጊዜ የፌዴራል ዳኞች በየምድብ ችሎቱ በተደራጁ ተረኛ ችሎቶች እየሰሩ መቆየታቸውን የገለፀው ፍርድ ቤቱ፥  በቤትና በቢሮ ለውሳኔ፤ ለብይንና ለትዕዛዝ የተቀጠሩ መዛግብትን በማቃለል ከፍተኛ ውጤት በማስገኘት ላይም መሆናቸውን አስታውቋል።

በተጨማሪም የተረኛ ዳኞችን ቁጥር በመጨመር ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር ተያይዞ የሚቀርቡላቸውን ጉዳዮች በመስራት ላይ እንዳሉና በተሰጡ ውሳኔዎች ላይ የሚቀርቡ የይግባኝ አቤቱታዎችም በየደረጃው ባሉ ፍርድ ቤቶች በመታየት ላይ ይገኛሉ ብሏል።

ወረርሽኝ በሃገራችን ስርጭቱ እንዳይስፋፋ ለመገደብ እየተደረገ ያለውን ጥረት ለማገዝና በየዕለቱ በትንሹ 18 ሺህ ያህል ባለጉዳዮች የሚስተናገዱባቸውን ፍርድ ቤቶች በከፊል ዝግ ማድረግ ባለጉዳዮች በቤት እንዲቆዩና አካላዊ ርቀትን እንዲጠብቁ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ከግንቦት 3/2012 ዓ.ም ጀምሮ ለ22 የስራ ቀናት ማለትም እስከ ግንቦት 30/2012 ዓ.ም ድረስ አሁንም ለሶስተኛ ዙር በከፊል ዝግ ሆነው እንዲቆዩ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ መወሰኑን ነው ያመለከተው።

በዚህ ጊዜ ውስጥም፦

* በየፍርድ ቤቱ ለምርመራ እና ለውሳኔ የተቀጠሩ ውዝፍ መዛግብት ተለይተውና እንደየሁኔታው ታይተው እልባት የሚሰጣቸው ሲሆን፥ ውዝፍ መዛግብት የሌለባቸው ችሎቶች ውዝፍ መዛግብት ያለባቸውን ችሎቶች እንዲያግዙ እንደሚደረግ፣

* በማረሚያ ቤት ያሉ ባለጉዳዮችን በተመለከተም ከማረሚያ ቤት አስተዳዳሪዎች ጋር በመወያየትና መርሃ ግብር በማዘጋጀት በቪዲዮ ኮንፈረንስ አገልግሎት ለመስጠት ጥረት እንደሚደረግ፣

* ፍርድ ለተሰጠባቸው ጉዳዮች በቂ የውሳኔ ግልባጮች ከወዲሁ ተዘጋጅተው ባለጉዳዮችን እንዲጠብቁ እንደሚደረግ፣

* ባለጉዳዮች በአካል ፍ/ቤት ቀርበው በመደበኛው አካሄድ የመሰማት እድል ሊሰጣቸው ይገባል የሚያስብሉ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ በሪጅስትራር ተለይተውና የሚመለከተውን አካል በማስፈቀድ ተግባራዊ የሚደረግ ይሆናል ብልሏል።

* አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈጸም ተግባራዊ እየተደረጉ ካሉ መመሪያዎች ጋር በተያያዘ የሚቀርቡ ጉዳዮች በአፋጣኝ እልባት ማግኘት የሚገባቸው በመሆኑ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በተረኛ ችሎቶች የዳኞች ቁጥር እንዲጨምር ይደረጋልም ነው ያለው።

ከእነዚህ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የሚቀርቡ የይግባኝ አቤቱታዎችም በአፋጣኝ ታይተው እልባት የሚሰጣቸው ይሆናል ብሏል።

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በሰጠው የስራ አቅጣጫ እጅግ አስገዳጅ አገራዊና ኢኮኖሚያዊ እንድምታ ያላቸው አስቸኳይ መፍትሄ ለሚፈልጉ ብርቱ ጉዳዮች እንደ ሁኔታው በየደረጃው የሚገኙ የፍ/ቤት አመራሮች እና የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር ኃላፊዎች ፈጣን ምላሽ እንዲሰጡ ነው ያሳሰበው።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.