Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያና ሀንጋሪ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያና ሀንጋሪ በፈረንጆቹ 1965 ዓ.ም ተፈርሞ በሥራ ላይ የነበረውን የአየር አገልግሎት ስምምነት በማሻሻል አዲስ የሁለትዮሽ የአየር አገልግሎት ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

የሁለቱ ሀገራት አየር መንገዶች በኢትዮጵያና በሀንጋሪ መካከል በሳምንት 7 የመንገደኛና ገደብ የሌለው የጭነት በረራ ማድረግ እንዲችሉ ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡

በተጨማሪም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሀንጋሪ ከሚያደርገው በረራ በተጨማሪ በመካከለኛ እና ከሀንጋሪ ባሻገር ወደ ሌሎች ሦስተኛ ሀገራት ገደብ የሌለው የጭነት በረራ እንዲሁም 3 ወደሚሆኑ የመካከለኛና ባሻገር ሀገራት የመንገደኛ በረራ በአምስተኛ ትራፊክ መብት ማድረግ የሚያስችለው ስምምነት ተደርጓል፡፡

ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ትልቅ የገበያ እድል እንደሚፈጥር ተስፋ የተጣለበት ይህ ስምምነት ከነሐሴ 8 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በጊዜያዊነት ተግባራዊ እንደሚሆን የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

ስምምነቱን የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው መንግሥቴ እና የሀንጋሪው አቻቸው ማቴ ሎዊንገር (ዶ/ር) ተፈራርመውታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.