Fana: At a Speed of Life!

የመቀሌና ራያ ዩኒቨርሲቲዎች ወደ መደበኛ ስራዎቻቸው እየተመለሱ ነው

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ተከስቶ በነበረው ግጭት ምክንያት የመማር ማስተማር ስራቸውን አቋርጠው የነበሩ የመቀሌና ራያ ዩኒቨርሲቲዎች ወደ መደበኛ ስራዎቻቸው እየተመለሱ መሆኑ ተገለጸ።

መቀሌ ዩኒቨርሲቲ 2 ሺህ እንዲሁም ራያ ዩኒቨርሲቲ 760 ትምህርታቸውን አቋርጠው የነበሩ ተማሪዎችን በመቀበል እያስተማሩ እንደሆነ ተጠቁሟል።

የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት አብዱልቃድር ከድር (ዶ/ር) እና የራያ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ነጋ አፈራ (ዶ/ር) ተቋማቱን ለመማር ማስተማር ስራው ዝግጁ በማድረግ ትምህርት መጀመሩን ገልጸዋል።

በትምህርት ሚኒስቴር የአስተዳደርና የመሰረተ ልማት ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ሰለሞን አብርሃ እንደገለጹት÷ በአካባቢው ሰላም መስፈኑን ተከትሎ ዩኒቨርሲቲዎች ወደ መማር ማስተማር ስራቸው እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡

ለዚህም የመማሪያ ክፍሎችን፣ የተማሪዎች ማደሪያዎችንና፣ ቤተ መጽሃፍትና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን ዝግጁ እንዲሆኑ በማድረግ ትምህርት መጀመሩን ነው የተናገሩት።

ተማሪዎችም በአካባቢው ሰላም ተመልሶ ትምህርት በመጀመሩ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡

በሲሳይ ዱላ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.