Fana: At a Speed of Life!

የሠላም ተመላሾች ያገኙትን ድጋፍ ተጠቅመው ራሳቸውን እና ሀገራቸውን መለወጥ አለባቸው- አቶ አሻድሊ ሃሰን

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሠላም ተመላሾች ያገኙትን ድጋፍ ተጠቅመው ራሳቸውን እና አገራቸውን በሥራ ለመለወጥ መትጋት እንዳለባቸው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሃሰን አስገነዘቡ::

በክልሉ ወደ ሠላማዊ ህይወት ተመላሽ የሆኑ ከ680 በላይ የጉሙዝ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉህዴን) ታጣቂዎች የተዘጋጀላቸውን የተሃድሶ ስልጠና አጠናቀው ዛሬ ተመርቀዋል::

የሠላም ተመላሾቹ በማዕድን ልማት ለማሰማራት የሚያስችሏቸው ከ45 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመቱ መሳሪያዎች ተበርክቶላቸዋል::

አቶ አሻድሊ ሃሰን በዚሁ ጊዜ እንዳሉት÷ የክልሉ መንግስት ለሠላም እና ልማት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው::

ባለፉት ዓመታት በተከሰተ የጸጥታ ችግር ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ያስታወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ ወጣቶቹ መንግስት ያደረገላቸውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው የትጥቅ ትግል በማቆም ወደ ሰላም በመመለሳቸው አድንቀዋል::

ወጣቶች በክልሉ ያለውን ሰፊ የወርቅ እና ለግብርና የሚውል ለም መሬት በአግባቡ በማልማት ራሳቸውን እና ሃገራቸውን ከድህነት ማላቀቅ አለባችሁ ማለታቸውንም ኢዜአ ዘግቧል።

ችግሮች ቢያጋጥሙ እንኳን በመነጋገር መፍታት እንደሚገባ ጠቅሰው÷ ለወደፊቱም የሠላም አማራጭ ከሚያደናቅፉ አሉባልታዎች ጆሮ ሳይሰጡ በስራ እንዲተጉ ጠይቀዋል::

የክልሉ መንግስት ለተገኘው ሠላም መቀጠል እና ለህብረተሠቡ ህይወት መለወጥ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አቶ አሻድሊ አስታውቀዋል::

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.