በአፋር ክልል የ45 ትምህርት ቤቶች ጥገና እየተከናወነ ነው
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፋር ክልል በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በነበረው ግጭት ውድመትና ከፊል ጉዳት ከደረሰባቸው 282 ትምህርት ቤቶች 45 በጥገና ላይ መሆናቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡
እስካሁን በተከናወነው ሥራ የ31 ትምህርት ቤቶች ጥገና ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት መሆናቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አሕመድ ያዬ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡
እንዲሁም በያዝነው የክረምት ወቅት የ14 ትምህርት ቤቶችን ግንባታ በማጠናቀቅ በመስከረም ወር 2016 ዓ.ም ለመማር ማስተማር ሥራ ዝግጁ እንዲሆኑ እተሠራ ነው ብለዋል፡፡
በግጭቱ ምክንያት 96 ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን እና 186 በከፊል መጎዳታቸውን አስታውሰዋል።
በሌላ በኩል በክልሉ ከሚገኙ 1 ሺህ 241 ትምህርት ቤቶች መካከል በሕብረተሰቡና ባለሀብቶች እገዛ የ123 ትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል እየተሠራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
በክልሉ ከሚገኙት 41 ወረዳዎች ከእያንዳንዳቸው ሦስት ትምህርት ቤቶች ደረጃቸውን እንዲያሻሽሉ አቅጣጫ መቀመጡንም ጠቁመዋል፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ የትምህርት መሠረተ ልማት ግንባታዎችና ማሻሻያ ንቅናቄን ሐምሌ 6 ቀን 2015 ዓ.ም ማስጀመራቸው ይታወሳል፡፡
በዮሐንስ ደርበው