በፀሎት መርሐ ግብሩ የታየው ትብብርና ትጋት የሀገሪቱን ችግር ለማስወገድ ትልቅ ኃይል ነው- ጠ/ሚ ዐቢይ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 27፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ለአንድ ወር በተከናወነው ፀሎት መርሐ ግብር የታየው ትብብርና ትጋት የሀገሪቱን ችግር ለዘለቄታው ለማስወገድ ከተጠቀምንበት ትልቅ ኃይል መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ገለፁ።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ለከአንድ ወር ሲከናወን የቆየው የፀሎት መርሃ ግብር መጠናቀቅን አስመልክተው በፌስቡክ ገፃቸው መልእክት አስተላልፈዋል።
በመልእክታቸውም “የኢትዮጵያ የሃይማኖት አባቶች ባዘዙት መሠረት ለአንድ ወር የተከናወነው የጸሎት መርሐ ግብር በዐርበኞች ቀን ተጠናቅቋል” ብለዋል።
“የጸሎት መርሐ ግብሩ ብዙ መንፈሳዊ ሀብቶች እንዳሉን አሳይቶናል። በጸሎት መርሐ ግብሩ ያሳየነውን ትብብርና ትጋት የዚህችን ሀገር ችግር ለዘለቄታው ለማስወገድ ከተጠቀምንበት ትልቅ ኃይል ነው” ሲሉም ገልፀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ፥ “መርሐ ግብሩን ያዘጋጁ፣ ያስተባበሩና በሚዲያ ያስተላለፉ ሁሉ ምስጋና ይገባቸዋል” ሲሉም በመልእክታቸው ገልፀዋል።
የኮሮና ቫይረስ በአለምና በሀገራችን መከሰትን ተከትሎ ባለፈው አንድ ወር ሲካሄድ የቆየው ሃገራዊ የፀሎት መርሃግብር ማጠቃለያ መርሃ ግብር በማካሄድ ተጠናቋል።
በፀሎት መርሃግብር ማጠቃለያ ላይ የሃይማኖት መሪዎች እና አባቶች እንዲሁም ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ተገኝተዋል።