81 ሰዎች በበጎ ፍቃደኝነት የዓይን ብሌናቸውን ለመለገስ ቃል ግቡ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) እየተካሄደ ያለውን የጤና ኤግዚቢሽን ከጎበኙ ሰዎች መካከል 81 ሰዎች በበጎ ፍቃደኝነት የዓይን ብሌናቸውን ለመለገስ ቃል ግቡ፡፡
በሳይንስ ሙዚየም በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና ተቋማት እየተጎበኘ ያለው የጤናው ዘርፍ ልማትን የሚያሳየው ዐውደ ርዕይ ከጉብኝቱ ጎን ለጎን የተለያዩ መርሐ ግብሮች እየተከናወኑበት ነው።
ከጎብኝዎች የበጎ ፍቃድ የሆኑ የደም ልገሳ እና የዓይን ብሌን ልገሳ ማሰባሰብ አንደኛው የሰብዓዊነት ተግባር እንደሆነም ተገልጿል፡፡
ከሰኔ 14 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ለህዝብ ይፋ የሆነው ኢግዚቢሽን እስከ ዛሬ ሐምሌ 13 ቀን 2015 ዓ.ም ባሉት ቀናትም 81 ሰዎች በበጎ ፍቃደኝነት የዓይን ብሌናቸውን ለመለገስ ቃል እንደገቡ የጤና ሚኒስቴር መረጃ አመልክቷል።
በኢትዮጵያ በዓይን ብሌን ጠባሳ ምክንያት በርካታ ወገኖች የዓይን ብርሃናቸውን አጥተው የሚኖሩ በመሆናቸው በሰብዓዊነት የዓይን ብሌን የመለገስ ሰብዓዊ ተግባርን ለመፈጸም ቃል እንግባ ሲል የጤና ሚኒስቴር ጥሪ አቅርቧል።