Fana: At a Speed of Life!

ከ12ኛ ክፍል ፈተና ጋር በተያያዘ በአለፈው ዓመት የተስተዋሉ ጉድለቶች በዚህ ዓመት ታርመዋል- አገልግሎቱ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ጋር በተያያዘ በአለፈው ዓመት የተስተዋሉ የተለያዩ እንከኖች በዚህኛው ዓመት መስተካከላቸውን የትምሕርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት አስታወቀ፡፡

ምዝገባው በማንዋል በመሆኑ ተፈጥሮ የነበረውን የተፈታኞች መረጃ አያያዝ ጥራት ጉድለት ለማረም ዘንድሮ ምዝገባው በበይነ መረብ መካሄዱን በአገልግሎቱ የፈተና አስተዳደር መሪ ሥራ አስፈጻሚ ወንድወሰን ኢየሱስ ወርቅ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ከዩኒቨርሲቲ ድልድል፣ ዝግጅት እና አቀባበል ጋር በተያያዘ እክሎች እንደነበሩ አስታውሰው÷ ዘንድሮ ችግሩ መቀረፉን አረጋግጠዋል፡፡

ካጋጠመው ጉድለት በመማር የፈተና ማስፈጸሚያ ማንዋል እና መመሪያውን በማዘጋጀት እና በመከለስ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር ስለመደረጉም አንስተዋል፡፡

ተፈታኞችን ማዘጋጀት አለመቻሉ ዋና ችግር እንደነበር ጠቅሰው፤ በዚህ ዓመት በቂ ዝግጅት ስለመደረጉ አንስተዋል፡፡

በዚህ ዓመት የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ለመውሰድ ከተመዘገቡት 869 ሺህ 802 ትክክለኛውን የምዝገባ ሂደት ያላሟሉ 1 ሺህ 213 ተፈታኞች ምዝገባ መሠረዙንም አመላክተዋል፡፡

ዘንድሮ በመደበኛ 667 ሺህ 483 እንዲሁም በግል፣ በማታ እና በርቀት 200 ሺህ 691 ተፈታኞች ፈተና ይወስዳሉ ያሉት አቶ ወንድሰን፤ ፈተናው በሁለት ዙር በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።

የመጀመሪያው ዙር ፈተና ከሐምሌ 19 እስከ 21 ቀን፤ ሁለተኛው ዙር ፈተና ደግሞ ከሐምሌ 25 እስከ 28 ቀን 2015 ዓ.ምእንደሚሰጥ አረጋግጠዋል፡፡

የማኅበራዊ ሣይንስ ተፈታኞች ከሐምሌ 16 እስከ 17 ቀን 2015 ዓ.ም ወደ ተመደቡበት ዩኒቨርሲቲ እንደሚገቡ እና ሐምሌ 18 ገለጻ እንደሚሰጥም ተናግረዋል፡፡

የተፈጥሮ ሣይንስ ተፈታኞች ከሐምሌ 22 እስከ 23 ቀን 2015 ዓ.ም ወደ ተመደቡበት ዩኒቨርሲቲ እንደሚገቡ እና ሐምሌ 24 ቀን ገለጻ እንደሚሰጣቸው አመላክተዋል፡፡

ተፈታኞች ፈተናውን በራሳቸው ጥረት እንዲሠሩ አሳስበው÷ በአለፈው ዓመት የፈተና ደንብ ጥሰት የፈጸሙ 17 ሺህ ተፈታኞች ውጤት ሙሉ በሙሉ መሠረዙን አስታውሰዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.