በሽብር ወንጀል የተከሰሱ 24 ተከሳሾች የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ተደርጎ ወደ ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ ትዕዛዝ ተሰጠ
አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 12 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ፍርድ ቤቱ በሽብር ወንጀል የተከሰሱትን እነ ዶ/ር ወንደወሰን አሰፋ እና መስከረም አበራን ጨምሮ 24 ተከሳሾች የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ወደ ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ ትዕዛዝ ሰጠ።
ትዕዛዙን የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የፀረ ሽብር ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።
ተከሳሶቹ የኢፌዴሪ የወንጀል ህግ አንቀፅ 32/1/ሀ/ለ/፣ 35 እና 38 እና የሽብር ወንጀልን ለመቆጣጠር እና ለመከላከል የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1176/ 2012 አንቀፅ 3 ንዑስ ቁጥር 2 ስር የተመለከተውን ድንጋጌ የህግ ክልከላ አለበት በሚል ነው ፍርድ ቤቱ የዋስትና መብት ጥያቄያቸውን ውድቅ ያደረገው።
ዐቃቤ ህግ በተከሳሾቹ ላይ ”መነሻችን አማራ መድረሻችን ኢትዮጵያ” በሚል የፖለቲካ እና የርዕዮት አላማ ለማራመድ በማሰብ ሀገሪቱን እያስተዳደረ ያለውን መንግስት በተለያየ ወታደራዊ ስልት እና ስትራቴጅ በመንደፍ፣ የአማራ ክልል የሚዋሰኑባቸውን መንገዶች መዝጋት፣ ህዝብን ማሸበር እና መንግስትን አስገድዶ ከስልጣን ማውረድ የሚሉ የሽብር ተግባር ድርጊቶችን ጠቅሶ በክሱ ላይ ማስፈሩ ይታወሳል።
በተለይም ዐቃቤ ህግ በክሱ ላይ ተፈፅሟል ባለው የሽብር ድርጊት እንቅስቃሴ የማህበራዊ አገልግሎት መቋረጡን እና አመጽ መነሳቱን ጠቅሶ በዚህ የሽብር ተግባር ደግሞ አጠቃላይ የ217 ሰዎች ህይወት ማለፉን፣ 297 ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድ እና ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን እንዲሁም 1 ቢሊየን 298 ሚሊየን 346 ሺህ 276 ብር በላይ በሚገመት ንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል በማለት በክሱ አስፍሯል።
ይህ በዐቃቤ ህግ የቀረበው ክስ በንባብ ለተከሳሾቹ ከተሰማ በኋላ የተከሳሽ ጠበቆች የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ጠይቀው ነበር።
ከሳሽ ዐቃቤ ህግ ተከሳሾቹ የተከሰሱበት የሽብር ወንጀል ድንጋጌ ዋስትና መብታቸውን የሚያስከለክል መሆኑ ጠቅሷል።
ዐቃቤ ህግ በምክንያትነት ያቀረበውን ተከሳሾቹ በዋና ወንጀል አድራጊነት እና በሚሰጠው ውጤት ተካፋይ በመሆን፣ የሽብር ድርጊት በቀጥታ በመምራት፣ በማደራጀት የተግባር ተሳትፎ መሰረት 217 ሰዎች ህይወት ያለፈበት እና የተከሰሱበት አንቀጽ ከ15 ዓመት በላይ የሚያስቀጣ ድንጋጌ መሆኑን በመጥቀስ የዋስትና ጥያቄያቸው በወ/መ/ስ/ህ ቁጥር 63 መሰረት ውድቅ ይደረግ በማለት ተከራክሯል።
የተከሳሽ ጠበቆች ደግሞ ተከሳሾቹ በቀረበባቸው የወንጀል ክስ በጋራ እንጅ እያንዳንዳቸው ሰው ገድለዋል ተብሎ የቀረበ ዝርዝር የለም በማለት ተከራክረዋል።
በተጨማሪም ጠበቆቹ በግል ደረጃ ሰው ገድለዋል ተብሎ ባልተጠቀሰበት ሁኔታ ላይ የዋስትና መብታቸው ሊከለከል አይገባም በማለት ተከራክረው ነበር።
በዚህ መነሻ የግራ ቀኙን ክርክር የተከታተለው ፍርድ ቤቱ የተከሳሾችን የዋስትና መብት ከተከሰሱበት ድንጋጌ አንጻር የህግ ክልከላ ያለበት መሆኑን ጠቅሶ ውድቅ አድርጓታል።
ተከሳሾቹ ወደ አዲስ አበባ ማረሚያ ቤት እንዲወርዱም ትዕዛዝ ሰጥቷል።
የአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት ለተከሳሾቹ በፍላሽ የተሰጠው የክስ የማስረጃ ለማየት እንዲችሉ እንዲያመቻች አዟል።
አራት ጋዜጠኞች በመገኛና ብዙሃን አዋጅ መሰረት የዋስትና መብታችን ሊታይ ይገባል ብለው የጠየቁ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ በሙያ ተሳትፎ ሳይሆን በሽብር ድርጊጊት ተሳትፎ ነው በማለት ውድቅ አድርጎታል፡፡
ከተከሳሾች መካከል ወንደሰን አሰፋ (ዶ/ር)፣መስከረም አበራ፣ መሰረት ቀለመወርቅ (ዶ/ር፣ ሲሳይ አውግቸው (ረ/ፕ)፣ ዳዊት በጋሻው፣ ገነት አስማማው፣ ጎበዜ ሲሳይ፣ መንበረ አለሙ፣ ተስፋዬ መኩሪያ፣ ማስረሻ እንየው፣ ታደሰ ወንዳይነው፣ አንደበት ተሻገር እና ዳዊት እባቡን ጨምሮ 24 ግለሰቦች በችሎት ተገኝተው በፍርድ ቤቱ የተሰጠውን ብይን ተከታትለዋል።
በታሪክ አዱኛ