አምባሳደር ምስጋኑ ከአየርላንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዋና ጸሐፊ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከአየርላንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዋና ጸሐፊ ጆሴፍ ሐኬት ጋር የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችል ውይይት አደረጉ።
የሁለቱን አገሮች የቆየ ወዳጅነት በአዲስ የአጋርነት መንፈስ ማጠናከር እንደሚገባ አምባሳደር ምስጋኑ በውይይቱ ወቅት መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመልክቷል።
ኢትዮጵያ የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት በሙሉ ቁርጠኝነት እየተገበረች እንደምትገኝ ያስረዱት አምባሳደር ምስጋኑ፤ አየርላንድ እየተካሄደ ያለውን የመልሶ ማቋምና መልሶ ግንባታ ስራ እንድትደግፍ ጠይቀዋል።
የአየርላንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዋና ጸሐፊ ጆሴፍ ሐኬት በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግስት ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የሚያደርገውን ጥረት አገራቸው እንደምትደግፍ አረጋግጠዋል።
ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት የሁለቱን አገሮች የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ትብብር እንደሚያጠናክረው አመልክተዋል።