የጋናው ፕሬዚዳንት የኢትዮጵያና የጋናን ግንኙነት የበለጠ ለማሳደግ ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋገጡ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የጋናው ፕሬዚዳንት ናና አዶ ዳንኩዋ አኩፎ አዶ የኢትዮጵያና የጋናን ግንኙነት የበለጠ ለማሳደግ እና ለማጠናከር ቁርጠኛ እና ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
በጋና የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆነው የተሾሙት አምባሳደር ተፈሪ ፍቅሬ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለጋና ፕሬዚዳንት ናና አዶ ዳንኩዋ አኩፎ አዶ አቅርበዋል።
አምባሳደር ተፈሪ በዚህ ጊዜ ÷ኢትዮጵያና ጋና በአፍሪካ አንጋፋና ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳላቸው በመጥቀስ ታሪካዊውን ግንኙነታቸውን የበለጠ ለማጠናከር ቁርጠኝነታቸውን ገልጸዋል።
በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት የተፈጠሩ እድሎችን ለመጠቀም የንግድና የኢንቨስትመንት ተሳትፎን ማስፋፋት አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት በመስጠት መናራቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ፣ በሰላምና ደኅንነት፣ እንዲሁም በማዕድን ኢንዱስትሪ እና በፋርማሲዩቲካልስ ዘርፍ ላይ የልምድ ልውውጥና የዕውቀት ሽግግር ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት አስፈላጊ መሆኑንም አንስተዋል።
ፕሬዚዳንት ናና አዶ ዳንኩዋ አኩፎ አዶ በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያና የጋናን ግንኙነት የበለጠ ለማሳደግ እና ለማጠናከር እንዲሁም አምባሳደሩን በጋና ቆይታቸው ለመደገፍ ቁርጠኛ እና ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።