በጤና ዐውደ-ርዕይ ከ3 ሺህ በላይ ሰዎች ነፃ ምርመራ እና ምክር ማግኘታቸው ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሳይንስ ሙዚየም በተዘጋጀው የጤና ዓውደ-ርዕይ እስካሁን ከ3 ሺህ በላይ ሰዎች ነፃ ምርመራ እና ምክር ማግኘታቸውን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ዐውደ-ርዕዩን እስካሁን ከጎበኙት መካከል 3 ሺህ 49 ሰዎች ነጻ የጤና ምርመራ ማግኘታቸው ነው የተገለጸው፡፡
ከተመረመሩት ሰዎች መካከል 567 ወይም 18 ነጥብ 5 በመቶ ያኅሉ ከዚህ ቀደም ያልታወቀ የደም ግፊት እንዳለባቸው በምርመራ ተረጋግጧል፡፡
61 ወይም 2 በመቶ ያኅሉ ሰዎች ደግሞ የስኳር ሕመም እንደተገኘባቸው ተጠቁሟል፡፡
የደም ግፊትና የስኳር ችግር ከታየባቸው ሰዎች መካከል 15 ሰዎች አስቸኳይ እርዳታ የሚፈልጉ ሆነው በመገኘታቸው ወደ ሆስፒታል በሪፈር መልክ መላካቸው ተገልጿል፡፡
ሚኒስቴሩ በዓውደ-ርዕዩ ከተወሰደው ልምድ በመነሳት ሰዎች ዘወትር የጤንነት ሁኔታቸውን ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ እንዲከታተሉ እና መደበኛ ምርመራና ምክር እንዲያገኙ አሳስቧል፡፡
በሳይንስ ሙዚየም በብሔራዊ ደረጃ የጤና ዓውደ ርዕዩ በይፋ ለሕዝብ ዕይታ ከቀረበ 20ኛ ቀኑን ይዟል፡፡