Fana: At a Speed of Life!

በ2015 ዓ.ም ከ1 ነጥብ 2 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን በላይ የአፈር ማዳበሪያ ግዢ ተፈጽሟል – መንግሥት

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አርሶ አደሩ የሚያነሳውን የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ጥያቄ ምላሸ ለመስጠት መንግስት በ2015 ዓ.ም ከ1 ነጥብ 2 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን በላይ የአፈር ማዳበሪያ ግዢ መፈጸሙን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ፡፡

መንግስት ለዓመቱ ገዥ እንዲፈጸም ካደረገው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ ከ669 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ የአፈር ማዳበሪያ ወደ አገር ውስጥ ተጓጉዞ ካለፈው ዓመት ከተረፈው 210 ሺህ ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ ጋር ተጨምሮ ከ879 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ ማዳበሪያ አቅርቧል ብሏል አገልግሎቱ፡፡

ወደ አገር ውስጥ ከገባውና ከተጓጓዘው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ 842 ሺህ ሜትሪክ ቶን የአፈር ማዳበሪያ ለሕብረት ሥራ ማህበራት መከፋፈሉንም ጠቁሟል፡፡

ወደ አርሶ አደሩ እጅ እንዲደርስ እየተደረገ ያለው የአፈር ማዳበሪያ መጠን ደግሞ 706 ሺህ ሜትሪክ ቶን መሆኑ ነው የተመለከተው፡፡

አሁንም 172 ሺህ ሜትሪክ ቶን የአፈር ማዳበሪያ በእጅ የሚገኝ መሆኑን አገልግሎቱ አረጋግጧል፡፡

ማዳበሪያው የሚፈለግበት የእርሻ ወቅት ሳያልፍ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ አካባቢዎችን በመለየት ማዳበሪያውን በፍጥነት ለማድረስ እየተሰራ መሆኑም ተመልክቷል፡፡

በተጨማሪም የአፈር ማዳበሪያ ጭነው ጅቡቲ ወደብ ከደረሱት 13 መርከቦች መካከል÷ በ5 መርከቦች የተጫነው የአፈር ማዳበሪያ በቅርቡ መጓጓዝ እንደሚጀምርም ተጠቁሟል፡፡

የግብአት አቅርቦት በሚፈለገው ልክ አለመድረስ ደግሞ በቀጣዩ አመት ሃገራዊ ምርትና ምርታማነት ላይ የራሱን ተፅእኖ ስለሚያሳርፍ÷ አርሶአደሩ በጊዜው የአፈር ማዳበሪያም ሆነ ሌሎች የግብርና አቅርቦቶች እንዲደርሱት ማድረግ በዚህ ዘርፍ ያሉ አካላት ቀዳሚ ሃላፊነት ነው ብሏል አገልግሎቱ፡፡

መንግስትም አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እያደረገ ስለመሆኑ ነው አገልግሎቱ ያረጋገጠው፡፡

እንዲሁም በዘርፉ ብልሹ አሰራር ያለባቸውና ተገቢው ግብአት ለአርሶ አደሩ እንዳይደርስ እንቅፋት የሆኑትን አካላት ተከታትሎ በቁጥጥር ስር የማዋል ተግባር በአንዳንድ ክልሎች ተጀምሯል ነው የተባለው፡፡

ይህ ተግባር በሁሉም ክልሎች የሚቀጥል ስለመሆኑም ተጠቅሷል፡፡

የበልግ እርሻ እንቅስቃሴ ስራን በተመለከተ÷ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በሲዳማ፤ በደቡብ እና ደቡብ ምዕራብ ክልሎች ከ2 ነጥብ 4 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት መታቀዱን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት መረጃ ያመላክታል፡፡

እስከ ሰኔ 11 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስም 2 ነጥብ 7 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት ታርሷል ተብሏል፡፡

ከዚህ ውስጥ 2 ነጥብ 6 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑም ተጠቁሟል፡፡

በኩታ ገጠም የታረሰ መሬትን በሚመለከት÷ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በሲዳማ እና በደቡብ ምዕራብ ክልሎች 4 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር መሬት ታርሶ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር በላይ በዘር ተሸፍኗል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.