የቱርክ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ለመሳተፍ ፍላጎት እንዳላቸው ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የቱርክ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ የተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ለመሳተፍ ፍላጎት እንዳላቸው በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ባርክ ባራን ገለፁ።
5ኛው አግሪ ፋድ እና የምግብ ማሸጊያ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
በንግድ ትርኢቱ ከተለያዩ አገራት የተወጣጡ ከ130 በላይ ኩባንያዎች ምርትና አገልግሎታቸውን ማቅረባቸው ተገልጿል፡፡
የቱርክ፣ የቻይና፣ የጀርመን፣ የኔዘርላንድስ፣ የሕንድ፣ የጣልያን፣ የኦስትሪያ፣ የቡልጋሪያ፣ የፈረንሳይ፣ የጀርመን፣ የጣሊያን፣ የጆርዳን፣ የኬንያ እና ሌሎችም ባለሃብቶች በንግድ ትርኢቱ ላይ ተሳትፈዋል።
በግብርና፣ በምግብ ማቀነባበሪያ፣ በፕላስቲክ፣ ሕትመትና የማሸጊያ ኢንዱስትሪዎች ላይ ባተኮረው የንግድ ትርኢት ከ18 በላይ የቱርክ ኩባንያዎች መሳተፋቸው ታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ባርክ ባራን÷ ኢትዮጵያና ቱርክ ለረጅም ዘመናት የዘለቀ ጠንካራ ወዳጅነት ያላቸው አገሮች ናቸው ብለዋል፡፡
ሁለቱ አገሮች በተለይም በንግድና የኢኮኖሚ ትስስር እንዲሁም በኢንቨስትመንት የላቀ የትበብር ግንኙነት ያላቸው መሆኑንም አንስተዋል፡፡
በርካታ የቱርከ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ የተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች መሳተፋቸውን አስታውሰው÷ ሌሎች በርካታ ባለሃብቶችም ለመሳተፍ ፍላጎት ማሳየታቸውን ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ በርካታ የኢንቨስትመንት አማራጮችና ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸውን አረጋግጠናል ያሉት አምባሳደሩ÷የአገራችን ባለሃብቶች አድሉን ለመጠቀም ዝግጁ ናቸው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ምርቶች በቱርክ ገበያ በስፋት እንዲተዋወቁና እንዲሸጡ እንሰራለን ሲሉም ማረጋገጣቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡