በሐረሪ ክልል በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከ2 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ችግኞች ይተከላሉ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረሪ ክልል በዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከ2 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ችግኞች እንደሚተከሉ የክልሉ የግብርና ልማት ቢሮ አስታውቋል።
የቢሮው ምክትል ሃላፊ ሻሜ አብዲ እንደገለጹት በዘንድሮ ክረምት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከ2 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ችግኞች ይተከላሉ።
ከሚተከሉት ችግኞች ውስጥ 70 በመቶው ለጥምር ደን እና ቀሪ 30 በመቶዎቹ ደግሞ ለደን ልማት እንደሚሆኑም ነው የተናገሩት፡፡
ችግኞችን መትከል ብቻ ሳይሆን በዘለቄታዊ መንገድ የመንከባከብና የመጠበቅ ስራ ማከናወን እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
ከችግኝ ተከላ ጋር በተያያዘ በገጠር እና በከተማ ወረዳዎች የአፈርና የውሃ ጥበቃ ስራ በሰፊው ሲከናወን መቆየቱን ሃላፊው ጠቁመዋል።
በክልሉ የቂሌ ኤረር ችግኝ ጣቢያ ሃላፊ አቶ ዘሪሁን አያሌው በበኩላቸው፥ በጣቢያው ለዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ ልማት ዝግጅት ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ የፍራፍሬና የደን ችግኞች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
በሐረሪ ክልል ባለፉት አራትዓመታት ከ10 ሚሊየን በላይ ችግኞች መተከላቸውን የክልሉ ኮሙኑኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡