Fana: At a Speed of Life!

በዲጂታል የመገበያያ ስርዓት ላይ ያተኮረ ሀገር አቀፍ ውይይት እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 12 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀገር አቀፍ የገበያ መረጃ ስርዓት ላይ ያተኮረ ሀገር አቀፍ ውይይት በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።

 

የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ከፌደራል ንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር እና በተዋረድ ከሚገኙ የከልል ንግድና የገበያ ልማት ቢሮዎች ጋር በመቀናጀት የመረጃ ስርአቱን አልምተውታል።

 

በአሁኑ ወቅት የዲጂታል መገበያያ ስርዓቱን የማልማት የመጀመሪያ ደረጃ ስራ ተጠናቆ የተጠቃሚዎች እና የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ በክልል ደረጃ በማዘጋጀት አስተያየቶችን የማሰባሰብ ስራ መከናወኑ ተገልጿል።

 

ሀገር አቀፍ ውይይቱም በፌደራል ደረጃ የሚገኙ ዋና ዋና ተጠቃሚዎች እና ቁልፍ ባለድርሻ አካላት እንዲሳተፉ ለማስቻል ነው እየተካሄደ ያለው::

 

የመረጃ ስርዓቱ ዋና ዓላማ ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አግባብነት ያለው የግብርና ምርቶች የገበያ መረጃ በግብይት ሰንሰለቱ ለሚገኙ ተዋናዮች በመስጠት ግብይታቸው በመረጃ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ለማስቻል እንደሆነ በውይይቱ ላይ ተገልጿል::

 

በዚህ መሰረት በአሁኑ ወቅት በ19 የግብርና ምርቶች ከ311 የገበያ ማዕከላት ሳምንታዊ የገበያ መረጃዎችን በመሰብሰብ እና ትክክለኛነታቸውን በማረጋገጥ ለተጠቃሚዎች በማሰራጨት ላይ ይገኛል ተብሏል::

 

ኢንስቲትዩቱ የገበያ መረጃ ከማሰራጨት በተጨማሪ የአምራቾችን የገበያ ዕድል ከማስፋት አንጻር አምራቾችን፥ አቅም ካላቸው ገዢዎች ጋር በቀጥታ የሚያገናኝ የዲጂታል የመገበያያ ስርዓት በማልማት ላይ ይገኛል፡:

 

 

 

በአዲሱ ሙሉነህ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.