በኢትዮጵያ ከኮሮና ቫይረስ ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 25 ደርሷል
አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 16 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ከኮሮና ቫይረስ ያገገሙት ሰዎች ቁጥር 25 መድረሱን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ አስታወቁ።
ሚኒስትሯ ባለፉት 24 ሰዓታት ለ933 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ የላቦራቶሪ ምርመራ መደረጉንም በፌስ ቡክ ገጻቸው አስታውቀዋል።
ቫይረሱ የተገኘባቸው የ60 ዓመት ሴትም ከኢንግሊዝ የመጡና በአስገዳጅ የለይቶ ማቆያ ውስጥ ያሉ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።
በዚህም አንድ ሰው ቫይረሱ እንደተገኘበት ጠቅሰው፥ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 117 መድረሱን ገልጸዋል።
እስካሁንም ከቫይረሱ 25 ሰዎች ማገገማቸውንም ነው ሚኒስትሯ ያስታወቁት።
ሚኒስትሯ አያይዘውም ትናንትና ዛሬ ምርመራ ከተደረገላቸው 1 ሺህ 898 ሰዎች መካከል 1 ሰው ላይ ብቻ ቫይረሱ መገኘቱ፥ የቫይረሱ ስርጭት መቀነሱንም ሆነ በሕብረተሰቡ ውስጥ የቫይረሱ ስርጭት አለመኖሩን የሚገልጽ አለመሆኑን መረዳት ያስፈልጋል ብለዋል።
እስካሁን ምርመራ የተደረገላቸው እና ቫይረሱ እንዳለባቸው የተገለፀው በአብዛኛው በአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ የነበሩና የተወሰኑት ደግሞ ቫይረሱ እንዳለባቸው ከታወቁ ሰዎች ጋር የቅርብ ንኪኪ የነበራቸው ሰዎች መሆናቸውን በመጠቆም።
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision