አቶ አደም ፋራህ የቻይና መንግስት ከፍተኛ የልኡካን ቡድንን ተቀብለው አነጋገሩ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ በቻይና የናንዣ ግዛት የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ሀላፊ በሆኑት በሚስተር ሊያንግ ሹን የተመራው የቻይና መንግስት ከፍተኛ የልኡካን ቡድንን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ።
ዘመናትን በተሻገረው የኢትዮ ቻይና ወዳጅነት ሁለቱ ሀገራት በተለያዩ መስኮች በትብብር መስራታቸውን ያነሱት አቶ አደም ፋራህ፥ ይህ ግንኙነት ወደተሻለ ደረጃ እንዲያድግ ብልፅግና ፓርቲ አተኩሮ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
ሁለቱ ሀገራት የፈጠሩት ግንኙነት ከውስጣዊ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት የፀዳ ፣ በመርህ ላይ የተመሰረተ እንዲሁም እኩልነትን መሰረት ያደረገ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
አሁናዊ በሆነው የሀገራችን የኢኮኖሚ ሁኔታ የቻይና የውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እየጨመረ መሆኑና በሀገራችን ላይ መዋዕለ ንዋያቸውን የሚያፈሱ የቻይና ኩባንያዎች ቁጥር እያደገ መሆኑን ነው የተናገሩት።
በሁለቱ ሀገራት ጠንካራ ግንኙነት ምክንያትም ኢትዮጵያ “ቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ”ን በመሰሉ የቻይና መንግስት የልማት ፕሮግራሞች ተጠቃሚ መሆን እንደቻለች አመልክተዋል።
ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ የገቢና ወጪ ንግድ የሚሳለጥበት የኢትዮ ጅቡቲ የባቡር መስመርንም ለአብነት ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያን በልማታዊ እንቅስቃሴዎች ከመደገፍ በላይ ብድሮችን በማራዘም እና የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማስፋት ቻይና አጋርነቷን እያሳየች እንደሆነ አንስተው ይህንንም ብልፅግና ፓርቲ ልዩ ቦታ እንደሚሰጠው ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት በቀኝ ግዛት ያልተገዛች እና ለመንግስታቱ ድርጅት ምስረታ ከፍተኛ አስተዋፆ እንደነበራትና ይህንንም በጎ ተፅእኖ በቀጣይ ለቻይና አፍሪካ ግንኙነት መዳበር እንደምትጠቀምበት አንስተዋል።
በቻይና የናንዣ ግዛት የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ሀላፊ የሆኑት ሚስተር ሊያንግ ሹን በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያን በሁለንተናዊ መልኩ ለመደገፍ የቻይና መንግስት ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የሲፒሲ እና የብልጽግና ፓርቲ ግንኙነት እንዲጠናከር፣ በመንግስታዊ ግንኙነቶችም ኢንቨስትመንቶች ፍሰታቸው እንዲያድግ፣ የንግድ አማራጮች እንዲሰፉ በቀጣይ ሰፊ ስራዎች በቻይና መንግስት በኩል እንደሚሰሩ ቃል መግባታቸውንም ከብልጽግና ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።