ለሊሴ ነሜ ከዱባይ ኢንቨስትመንት ፓርክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ለሊሴ ነሜ ከዱባይ ኢንቨስትመንት ፓርክ (ዲ አይ ፒ) ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኦማር አል መስማር ጋር ተወያይተዋል፡፡
ኮሚሽነሯ በውይይቱ ኩባንያው በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ መንደር ለመገንባት ስላለው እቅድ እና አተገባበር ዙሪያ መክረዋል፡፡
(ዲ አይ ፒ) በዱባይ ኢንቨስትመንት ኩባንያ የሚተዳደር በ2 ሺህ 300 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ የኢንዱስትሪ፣ የንግድ እና የመኖሪያ የተቀናጀ መንደር መሆኑ ተገልጿል፡፡
ሥራ አስፈጻሚው በውይይታቸው የኩባንያቸው እናት ድርጅት “ዱባይ ኢንቨስትመንት” በጆርጂያ፣ ግብፅ፣ ሞሮኮ እና አንጎላ ተመሳሳይ ፓርኮችን እያለማ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በቀጣይም በኩባንያው ሥር የሚገኙ ቅርንጫፎች ኢንቨስትመንታቸውን ለማስፋት ባላቸው እቅድ መሰረት ተጨማሪ ፓርክ ለማልማት ኢትዮጵያ ተመራጭ መሆኗን አብራርተዋል፡፡
ኮሚሽነሯ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ እንዲተገበር በመንግስት በኩል አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግላቸው መግለፃቸውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡