በፋና እና በእስራኤል የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጣቢያ የተሰናዳው የስልጠና መርሀ ግብር ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እና በእስራኤል የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጣቢያ በጋራ የተዘጋጀው ስልጠና ተጀመረ፡፡
ስልጠናው በተለይም በዶክመንተሪ ፊልም አዘገጃጀት ላይ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የካሜራ፣ የፕሮዳክሽን ዳይሬክተር እና ለዶክመንተሪ ባለሙያዎች የሚሰጥ ነው።
“ፋና ቤታችን ነው” ያሉት በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አለልኝ አድማሱ፥ ከዚህ ቀደም ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ለእይታ ያቀረባቸው ስራዎች በማንሳት አድናቆታቸውን ገልፀዋል።
የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በተለያዩ መንገዶች የማጠናከር ስራ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው በበኩላቸው፥ ስልጠናው የኢትዮጵያን እና የእስራኤልን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዛሬ የተጀመረው ስልጠናም የሁለቱን ሀገራት የህዝብ ለህዝብ እና የመንግስት ለመንግስት ግንኙነቶችን የሚያጠናክሩ የሚዲያ ስራዎችን በጥራት እና በብዛት ለመስራት እንደሚያስችል ነው ያመለከቱት።
በእስራኤል የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጣቢያ መስራች እና ስራ አስኪያጅ አቶ ፋሲል ለገሰ በበኩላቸው ፥ መሰል ስልጠና ከዚህ ቀደም ከተለያዩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ጋር መሰጠቱን በማስታወስ ተመሳሳይ ስልጠናዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
በፍቅርተ ከበደ