ሲሚንቶን ከተተመነው ዋጋ በላይ በሚሸጡት ላይ እርምጃ ሊወሰድ ነው
አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 26 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የሲሚንቶ ምርት ላይ ከተተመነው ዋጋ በላይ በሚሸጡ አከፋፋዮች እና ችርቻሮ የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አስታወቀ፡፡
የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በከተማዋ የሚታዩ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪዎችን ለመከላከል የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ እንደሆነ የንግድ ቢሮ ገልጿል፡፡
በዚህም ቢሮው በሲሚንቶ ምርት ላይ ከተተመነው ዋጋ በላይ በሚሸጡ የንግድ ድርጅቶች ላይ ከማሸግ ጀምሮ ሌሎች ህጋዊ እርምጃዎችን እንደሚወስድ አስታውቋል፡፡
ህብረተሰቡ በተለይም ሸማቾች ከተተመነው ዋጋ በላይ ከፍለው መሸመት እንደሌለባቸው የገለጸው ቢሮው ጉዳዩ ሲያጋጥማቸው በነፃ የስልክ ቁጥር 8588 በመደወል ጥቆማ አድርሱኝ ብሏል፡፡
ለዚህም የሲሚንቶ መሸጫ ዋጋው በዝርዝር ፦ ደርባ 1 ሺህ 68 ብር ከ36 ሳንቲም፣ ዳንጎቴ 1 ሺህ 106 ብር ከ85 ሳንቲም፣ ሃበሻ ሲሚንቶ 1 ሺህ 305 ብር፣ ኢትዮ 1 ሺህ 56 ብር ከ80 ሳንቲም፣ ሙገር 1 ሺህ 16 ብር ከ52 ሳንቲም፣ ናሽናል ሲሚንቶ 1 ሺህ 169 ብር ከ98 ሳንቲም፣ ካፒታል 1 ሺህ 101 ብር ከ05 ሳንቲም ሆኖ መተመኑን ከቢሮው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡