Fana: At a Speed of Life!

አቶ ግርማ የሺጥላ ማን ናቸው?

አቶ ግርማ የሺጥላ ወ/ጻዲቅ ከእናታቸው ከወይዘሮ ዘውዴ ስመኝ  ከአባታቸው ከአቶ የሺጥላ ወልደጻዲቅ በቀድሞው ሸዋ ክፍለ ሃገር በመንዝና ግሼ አውራጃ በጌራ ምድር ወረዳ  መሃል ሜዳ ከተማ ህዳር 17 ቀን 1967 ዓ.ም ተወለዱ፡፡

ዕድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰ የአንደኛና መለስተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በመሀል ሜዳ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ማጠናቀቅ ችለዋል፡፡

ገና በአፍላ ወጣት ዕድሜያቸው ከሰኔ 1986 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በአንጾኪያ ወረዳ የተፈጥሮ ሃብት ጽህፈት ቤት የስራ ባልደረባ በመሆን የመንግስትን ስራ አሀዱ ብለው ጀምረዋል፡፡

አቶ ግርማ የሺጥላ በወጣትነታቸው ባሳዩት ትጋትና ታታሪነት ምክንያት ለኃላፊነት የታጩ ሲሆን ከ1989 ዓ.ም እስከ 1990 ዓ.ም ድረስ በአማራ ብሔራዊ ክልል መንግስት በሰሜን ሸዋ ዞን የአንጾኪያ ወረዳ የኢኮኖሚ ዘርፍ ስራ አስፈጻሚ በመሆን ህዝባቸውና መንግስት የጣለባቸውን ኀላፊነት ተወጥተዋል፡፡

አቶ ግርማ የሺጥላ ለትምህርት በነበራቸው ልዩ ጉጉትና ፍላጎት ምክንያት የትምህርት ዕድል እንዲመቻችላቸው ዘወትር ጥያቄ ያቀርቡ ስለነበረ የተሰጣቸውን የመንግስትና የህዝብ ኃላፊነት ከማከናወን ጎን ለጎን ከግል ኮሌጅ በማኔጅመንት በዲፕሎማ ተመርቀዋል፡፡

አቶ ግርማ የሺጥላ በነበራቸው የስራ ታታሪነትና አስተዋይነት እንዲሁም ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በሚያገለግሉት ማህረሰብ ከፍ ያለ ተቀባይነት ስለነበራቸው ከ1990 ዓ.ም እስከ መስከረም ወር 1995 ዓ.ም ድረስ የአንጾኪያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ በመሆንም አገልግለዋል፡፡

አቶ ግርማ የሺጥላ በታችኛው እርከን በነበራቸው የአመራር ብቃትና ልዩ ተሰጥኦና ልምድ ምክንያት ለዞን ከፍተኛ ኃላፊነት ተመርጠው ወደ ሰሜን ሽዋ ዞን በመዛወር ከፍ ያሉ ኀላፊነቶችን ሲወጡ ኖረዋል፡፡

ከጥቅምት ወር 1995 ዓ.ም ጀምሮ የሰ/ሸ/ዋ ዞን ብአዴን ጽህፈት ቤት ኃላፊ በመሆን ቀጥለውም  ከመስከረም 1997 ዓ.ም  እስከ  ህዳር 30 ቀን 1998 ዓ.ም ድረስ  በሰ/ሸዋ ዞን የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደደር ምክትል ከንቲባና የማስታወቂያ ጽ/ቤት ኃላፊ በመሆን የከተማውን ህዝብ አገልግለዋል፡፡

በኋላም ከታህሳስ 01 ቀን 1998 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በሰሜን ሸዋ ዞን የባሶና ወራና ወረዳ ማስታወቂያ ጽኅፈት ቤት ኃለፊ በመሆን በየደረጃው የተሰጣቸውን ኃላፊነት በብቃት ብስለት እና በትጋት ከተወጡ በኋላ እንደገና ተመልሰው ከሚያዚያ 01 ቀን 1999 ዓ.ም እስከ መስከረም 2000 ዓ.ም ድረስ የሰሜን ሸዋ ዞን የህዝብ ግንኙነት አማካሪ በመሆን አገልግለዋል፡፡

አቶ ግርማ የሽጥላ በደብረብረሃን ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን  አግኝተዋል፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ካገኙ በኋላ  ወደ ስራ በመመለስ  የሰሜን ሸዋ ዞን ብአዴን አደረጃጀት እንዲሁም እስከ መስከረም 30 ቀን 2008 ዓ.ም ድረስ  የሰሜን ሸዋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ በመሆን የተሰጣቸውን የስራ ኀላፊነት በብቃት ተወጥተዋል፡፡

አቶ ግርማ የሽጥላ ከጥቅምት 01 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ በመሆን ካገለገሉ በኋላ ለከፍተኛ ትምህርት ወደአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመሄድ ትምህርታቸውን ጀምረዋል፡፡ በአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ ማለትም በኮተቤ ሜትሮ ፖሊቲያን  ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሲማሩ ቆይተው በኢኮኖሚክስ ተመርቀዋል፡፡

የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቸውን እንዳጠናቀቁ ከመስከረም 2013 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የኢንቨሲትመንት ቢሮ ኃላፊ በመሆን የክልሉን ህዝብና መንግስት በትጋት አገልግለዋል፡፡

አቶ ግርማ የሽጥላ ከመስከረም 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ህይወታቸውን በድንገተኛ አደጋ እስከተነጠቁበት ሚያዝያ 19 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ የብልጽግና ማዕከላዊ ኮሚቴ ስራ አስፈጻሚና የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ  ጽ/ቤት ሃላፊ በመሆን አገልግለዋል፡፡

አቶ ግርማ የሺጥላ በስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ በባሶና ወራና ወረዳ የቀይት ምርጫ ጣቢያ የክልል ምክር ቤት ዕጩ በመሆን ተወዳድረው ህዝቡ የሰጣቸውን ውክልና በኃላፊነት ስሜት ሲወጡ ቆይተዋል፡፡

የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስትንና የክልሉን ህዝብ ወክለው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የፌደሬሽን ምክር ቤት አባል በመሆን  የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ሲወጡ የቆዩ ወሳኝ አመራር ነበሩ፡፡

አቶ ግርማ የሽጥላ ከመደበኛ ስራ በተጓዳኝ የደብረብረሃን ዩኒቨርሲቲ ስራ አመራር ቦርድ አባል ሆነው ያገለገሉ ሲሆን የደብረ ብርሃን  ሪፈራል ሆስፒቴል ስራ አመራር ቦርድን እና የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ስራ አመራር ቦርድን በሰብሳቢነት መርተዋል፡፡

አቶ ግርማ የሺጥላ ከልጅነት እስከ እውቀት በተለያዩ የስራ ኃላፊነቶች ተመድበው ሲሰሩ መቆየታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ወዲህ በተደጋጋሚ የተከፈተብንን ጦርነት ለመቀልበስ ጉልህ ድርሻ ነበራቸው፡፡

በተለይም በሁለተኛውና በሦስተኛው ጦርነት ወቅት የሀገር ሉዓላዊነትን ለማስከበር ግንባር ቀደም መሪ በመሆን እስከ ውጊያ ወረዳ ድረስ በመግባት የክልሉ ህዝብ የተቃጣበትን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ ራሳቸውን ለመስዋዕትነት አዘጋጅተው ከፍተኛ አሰተዋጽኦ ያበረከቱ ቅንና አስተዋይ መሪ ነበሩ፡፡

አቶ ግርማ የሺጥላ ከ25 ዓመታት በላይ የክልሉን መንግስትና ህዝብ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ያለመታከት ማገልገላቸው የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ከወጣትነት እድሚያቸው ጀምሮ ህይወታቸውን በግፍ እስከተነጠቁበት ቀን ድረስ ራሳቸውን ለክልሉ ህዝብ ጥቅም በግንባር ቀደምነት አሰልፈው ደፋር አመራር አረጋግጠዋል፡፡

አቶ ግርማ የሽጥላ ብርቱ፣ ታታሪና ለቆሙለት አላማ ግንባራቸውን የማያጥፉ፣ የተሰጣቸውን ኃላፊነት የሚያከብሩ፣ ለአማራ ህዝብም ሆነ በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ህዝብ ሳይታክቱ የደከሙና ብልህና አዋቂ የህዝብ መሪ እንደሆኑ አብረዋቸው የሰሩ የስራ ባልደረቦቻው ሁሉ ይመሰክራሉ፡፡

አቶ ግርማ የሽጥላ ለስራ በወጡበት ወቅት የክልሉን ህዝብ ጥቅም ዛሬም ሆነ ዘወትር የማምከን ህልምና ትልም አንግበው ከሚንቀሳቀሱ ጸረ ህዝብ ኃይሎች ድንገት በተተኮሰባቸው ጥይት ሚያዝያ 19 ቀን 2015 ዓ.ም በተወለዱ በ48 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡

አቶ ግርማ የሺጥላ ባለትዳርና የሶስት ሴት እና የአራት ወንድ ልጆች አባት ነበሩ፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.