ከ749 ሚሊየን ብር በላይ በሀሰተኛ ደረሰኝ የተጭበረበረ ገቢ እንዲከፈል ማድረጉን የአማራ ገቢዎች ቢሮ ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ749 ሚሊየን 635 ሺህ ብር በላይ በሀሰተኛ ደረሰኝ የተጭበረበረ የመንግስት ገቢ እንዲከፈል ማድረጉን የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ገለጸ፡፡
በቢሮው የግብር ትምህርት እና ኮሙኒኬሽን የሥራ ሂደት ዳይሬክተር አቶ አግማስ ጫኔ እንደገለጹት÷ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ1 ሺህ 418 ግብር ከፋዮች 2 ሺህ 914 የሀሰተኛ ደረሰኝ ማግኘት ተችሏል፡፡
ቢሮው ባከናወነው የክትትል ስራም 749 ሚሊየን 635 ሺህ 754 ብር ለመንግስት ገቢ ማድረግ መቻሉን አንስተዋል፡፡
የግብር ሥወራና ማጭበርበር ችግርን ለመከላከል መሥሪያ ቤቱ የተለያዩ ሥልቶችን ነድፎ ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
ቢሮው የተጠናከር የክትትል ቡድን አደራጅቶ እየተከታተለ መሆኑን ጠቅሰው÷የታክስ ኢንተለጀንስና የኦዲት ምርመራ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ዳይሬክተሩ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ችግር የተገኘባቸው ተቋማት ላይ አስተዳደራዊና ሕጋዊ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
ከሶስተኛ ወገን 539 ጥቆማዎች ለገቢ ተቋሙ ደርሰው 495 ጥቆማዎችን በማጣራት 100 ሚሊየን 791 ሺህ 457 ብር ገቢ ማግኘት መቻሉን አስታውሰዋል፡፡
የስራ ግብር በማይከፍሉ 837 የግል ድርጅቶች ላይ በተደረገ ክትትል 158 ሚሊየን 128 ሺህ 372 ብር የስራ ግብር ገቢ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡
በየሻምበል ምህረት