በህገ-ወጥ መንገድ የተከማቸ የጨው ምርት ተያዘ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)በመዲናዋ የዋጋ ንረትን ለማባባስ በህገ-ወጥ መንገድ በከፍተኛ ደረጃ የተከማቸ የጨው ምርት መያዙን የፖሊስ የምርመራ ቡድን አስታውቋል፡፡
በጉዳዩ የተጠረጠረው አቶ ታደለ አበባው ደስታ የተባለ ግለሰብ ሆን ብሎ በጨው ምርት ገበያ ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እንዲከሰት በህገ-ወጥ መንገድ በአዲስ አበባ ከተማ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ልዩ ቦታው ቃሊቲ ገብርኤል አካባቢና ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ኃይሌ ጋርመንት እና በሸገር ከተማ ገላን ጉዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 በሚገኙ ትልልቅ መጋዘኖች ከፍተኛ የጨው ምርት ማከማቸቱ ተደርሶበታል ነው የተባለው፡፡
በዚህም ስለ ክምችቱ ከህዝብ የተሰጠውን ጥቆማ መነሻ በማድረግ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከኢትዮጵያ ጉሙሩክ ኮሚሽን ጋር ባካሄደው የተቀናጀ ኦፕሬሽን መጠኑ ከፍተኛ የሆነ የጨው ምርት ክምችት መያዙ ተገልጿል፡፡
በጥቆማው መሠረት በህገ-ወጥ መንገድ የተከማቸው የጨው ምርት የዋጋ ንረት ለማስከተል ሆን ተብሎ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑ፤ከዛም ባለፈ በአጠቃላይ ከፍተኛ ታክስ ማጭበርበር ጋር የተገናኙ በርካታ መረጃዎች መቅረቡም ተጠቁሟል፡፡
የጨው ምርቱና ክምችቱ ለተጠቃሚው ጤና ተስማሚ ባልሆነ መልኩ ስለመዘጋጀቱም የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡
ጨዉን በማዘጋጀትና በማከማቸት ሂደት ውስጥም ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸው አንዳንድ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በጥቅም ትስስር የተገናኙ በመሆኑን የቀረበው መረጃ ያመላክታል፡፡
የጨው ክምችቱ የተያዘ ሲሆን ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸው ተጠርጣሪዎች ላይም ጠንካራ ምርመራ መቀጠሉን የምርመራ ቡድኑ አስታውቋል።
ፌደራል ፖሊስ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መረጃ በቀጣይ የሚደርስበትን የምርመራ ውጤት ለህዝቡ ይፋ እንደሚደረግ የተመላከተ ሲሆን÷ ኅብረተሰቡ የተለመደውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠይቋል፡፡