ሀንጋሪ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሻሻል እንደምትሰራ አረጋገጠች
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)ሀንጋሪ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የንግድ ግንኙነት ለማሻሻል እንደምትሰራ ገለፀች፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ በሀንጋሪ የውጭ ጉዳይና የንግድ ሚኒስትር ፒተር ሲያርቶ ከተመራው የሀንጋሪ ልኡክ ጋር ተወያይተዋል፡፡
አቶ ገብረመስቀል በውይይቱ ÷የሁለቱ ሀገራት የንግድ ግንኙነት ክፍተት ያለበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በዚህም የሁለትዮሽ ንግዱን ለማሳለጥ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን በማመቻቸት የሁለቱን ሀገራት የንግድ ግንኙነትን ይበልጥ ለማጠናከር እና የንግድ ሚዛን ክፍተቱን ለማጥበብ እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡
የሀንጋሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የንግድ ሚኒስትር ፒተር ሲያርቶ በበኩላቸው÷ ሀንጋሪ የግብርና ምርቶችን ከኢትዮጵያ በማስገባት የሁለቱን ሀገራት የንግድ ግንኙነት ለማሻሻል እንደምትሰራ መናገራቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የሀንጋሪ ባለሀብቶችና ድርጅቶችም ኢትዮጵያ ውስጥ በግብርና፣ በውሃ፣ በአረንጓዴ ኢነርጂ፣በሶፍት ዌር ልማትና በምርጥ ዘር ልማት ዘርፍ በማሰማራት የሁለቱን ሀገራት የንግድ ግንኙነትና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ሀገራቸው ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል፡፡