የዓለም ባንክ በበጀት ድጋፍና በብድር መልክ ጠንካራ ድጋፍ ለኢትዮጵያ እንደሚያደርግ አረጋገጠ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ከዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት ዴቪድ ማልፓስ ጋር ተወያዩ።
በዚህም ወቅት በኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።
ፕሬዚዳንቱ የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት በመተግበሩ የኢትዮጵያ መንግስት ያሳካውን በማንሳት በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ ጥረቱ እንዲቀጥል አበረታተዋል።
በተጨማሪም በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት ፈተና የሆኑ ተግዳሮቶችን በማንሳት የተወያዩ ሲሆን፥ በኢትዮጵያ በማክሮ ኢኮኖሚ ደረጃ መረጋጋት ማምጣት እንደሚያስፈልግ ነው ያስረዱት።
በግጭት፣ ድርቅ እና ሀገሪቱ ያለባት እዳ ባመጣው መዋቅራዊ ችግር ለተነካው ኢኮኖሚ ፈጣን ማሻሻያ ማድረግ ጠቃሚ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት ለማምጣት እና ድህነትን ለመቀነስ ጠንካራ የማሻሻያ ፕሮግራም እየተገበረ እንደመሆኑም የዓለም ባንክ በበጀት ድጋፍና በብድር መልክ ጠንካራ ድጋፍ ለኢትዮጵያ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።