ሙሉቀን ሐብቱን (ዶ/ር) ጨምሮ 5 ተከሳሾች በነፃ እንዲሰናበቱ ፍርድ ቤቱ ወሠነ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ የቴክኒክ ሙያ ሥልጠናና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ የነበሩት ሙሉቀን ሐብቱን (ዶ/ር) ጨምሮ አምሥት ተከሳሾች በነፃ እንዲሰናበቱ ፍርድ ቤቱ ወሰነ።
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በኮንዶሚኒየም ዕጣ ማጭበርበር ክስ የተመሰረተባቸው ተከሳሾች ላይ ብይን ሰጥቷል።
ከ3ኛ ዙር የ40/60 እና ከ14ኛ ዙር የ20 /80 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ መጭበርበር ጋር ተያይዞ ክስ ከተመሰረተባቸው 11 ተከሳሾች ውስጥ ነው አምስት ተከሳሾች በነፃ እንዲወጡ የተወሰነው።
ዐቃቤ-ሕግ በ11 ግለሰቦች ላይ ሦስት ክሶችን መስርቶ የሰው እና የሠነድ ማስረጃዎችን ለፍርድ ቤቱ አቅርቦ ነበር።
በተከሳሾቹ ላይ የቀረበውን የዐቃቤ- ሕግ የሰው እና የሠነድ ማስረጃ የመረመረው ፍርድ ቤቱ÷ዛሬ 1ኛ ተከሳሽ ሙሉቀን ሐብቱን (ዶ/ር)፣ 2ኛ ተከሳሽ አብርሃም ሰርሜሎን ጨምሮ አምሥት ተከሳሾች በነፃ እንዲሰናበቱ ወስኗል።
ሌሎቹ አምሥት ተከሳሾች ደግሞ የጠየቁት የዋስትና መብት ተከብሮላቸው እንዲከላከሉ ነው ትዕዛዝ የተሰጠው።
10ኛ ተከሳሽን በሚመለከትም በሌለበት ጥፋተኛ ተብሏል።
8ኛ እና 9ኛ ተከሳሾች በ80 ሺህ ብር ፣ 4ኛ ፣ 5ኛ እና 7ኛ ተከሳሾች ደግሞ በ 50 ሺህ ብር ዋስ ከእስር እንዲፈቱ ፍርድ ቤቱ ዛሬ ከሰዓት በነበረው ችሎት አዟል።
ከግንቦት 2 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ባሉ ሦስት ተከታታይ ቀናት የአምሥቱን ተከሳሾች የመከላከያ ምስክሮች ቃል ለመስማት ፍርድ ቤቱ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በዙፋን ካሳሁን