በደቡብ ኮሪያ ምርጫ የፕሬዚዳንት ሙንጄይ ኢን ፓርቲ ማሸነፉ ተነገረ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 8፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በደቡብ ኮሪያ በተካሄደው የፓርላማ ምርጫ የፕሬዚዳንት ሙንጄይ ኢን ፓርቲ ማሸነፉ ተነገረ።
ደቡብ ኮሪያ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በዓለማችን ላይ ከተከሰተ በኋላ ምርጫ ያደረገች የመጀመሪያዋ ሀገር መሆና ይታወቃል።
በጣም ከፍተኛ ጥንቃቄ እና አካላዊ መራራቅ ተግባራዊ በተደረገበት የሀገሪቱ የምክር ቤት ምርጫም የሀገሪቱን የሚያስተዳድረው የፕሬዚዳንት ሙንጄይ ኢን ፓርቲ ማሸነፉም ታውቋል።
የፕሬዚዳንት ሙንጄይ ኢን ፓርቲ ምርጫውን እንዲያሸንፍ ካደረጉት ውስጥም የሀገሪቱ መንግስት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል በሚሰራው ስራ ከህዝቡ ድጋፍ በማግኘቱ ነው ተብሏል።
እስካሁን በተደረገው የድምጽ ቆጠራም የፕሬዚዳንት ሙንጄይ ኢን ዴሞክራቲክ ፓርቲ ከ300 የብሄራዊ ምክር ቤት መቀመጫ ውስጥ 173 ማሸነፉን አረጋጧል።
የዴሞክራቲክ ፓርቲ እህት የሆነው ፕላትፎርም ፓርቲ ደግሞ 17 መቀመጫዎችን እንደሚያሸንፍ የተገመተ ሲሆን፥ ይህም መንግስት በብሄራዊ ምክር ቤቱ የሚኖረውን የመቀመጫ ቁጭር 180 ያደርሰዋል ነው የተባለው።
በምርጫው ላይ ከፍተኛ ድምጽ ካገኙት ውስጥ ከዚህ ቀደም በለንደን የሰሜን ኮሪያ ኤምባሲ ውስጥ በዲፕሎማትነት ያገለገሉት እና ከሰሜን ኮሪያ ኮብልለው ወደ ደቡብ ኮሪያ የገቡት ታሄ ያንግ ሆ አንዱ ናቸው።
ከሰሜን ኮሪያ ኮብልለው ወደ ደቡብ ኮሪያ የገቡት ታሄ ያንግ ሆ በሴኡል ግዛት ውስጥ በምትገኘው ጋንጋናም ላይ ነው በማሸነፍ የምክር ቤት አባል የሚያደርጋቸውን ድምጽ ያገኙት።
ምንጭ፦ ቢቢሲ