ከፀሐይ ክብደት 30 ቢሊየን እጥፍ የገዘፈ በርባኖስ ተገኘ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)በአፅናፈ-ሰማይ ላይ ከተዘረጉ በርካታ “ጋላክሲዎች” ይልቅ የገዘፈ በርባኖስ ወይም ጥልቁ ጥቁር ጉድጓድ “ብላክ ሆል” መገኘቱን የእንግሊዝ ተመራማሪዎች አስታወቁ።
በዶክተር ጀምስ ናይቲንጌል የተመራው የእንግሊዙ ዱርሃም ዩኒቨርሲቲ የጥናት ቡድን ያገኘው በርባኖስ የፀሐይን ክብደት በ30 ቢሊየን ጊዜ እጥፍ የሚልቅ እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡
ተመራማሪወቹ ይህን ያክል መጠን ያለው በርባኖስ መገኘቱን እንግዳ እንደሆነባቸውም ነው የጥናት ቡድኑ መሪ የሚናገሩት።
በህዋ ላይ ከሚገኙ አካላት በመጠኑ ትልቁ ነው የተባለው ይህ በርባኖስ እንደ ሚልክዌይ (ፀሐይን ጨምሮ የፕላኔቶችን ስብስብ በያዘው) ጋላክሲ ባሉ ትላልቅ ጋላክሲዎች መሃል ላይ እንደሚገኝም ይታመናል።
የበርባኖሱ ግኝት ከዳር እንዲደርስ ሂደቱን በማሳለጥ ረገድ የጀርመኑ ማክስ ፕላንክ ኢንስቲትዩት ድጋፍ ማድረጉ ተነግሯል፡፡
በተጨማሪም የናሳው “ሃብል ቴሌስኮፕ” ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን ምሥሎች በማንሳት እና ትርጉም እንዲያገኙ ለዱርሃም ዩኒቨርሲቲ በመላክ በሱፐር ኮምፒዩተር በርባኖሱ መኖሩ ተረጋግጧል፡፡
ጥናቱ ትናንትና ይፋ የሆነው በሮያል የሥነ-ፈለክ ማኅበር መሆኑንም አር ቲ ዘግቧል፡፡
በርባኖስ ወይም በእንግሊዝኛው አጠራር “ብላክ ሆል” በኅዋ ላይ ያለ ጥልቅ ጉድጓድ ሲሆን ከፍተኛ የስበት ኃይል ያለውና ብርሃን እንዳይታይ አድርጎ የማስቀረት ዐቅም ያለው መሆኑን የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች ይገልጻሉ።