ከ124 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመቱ የኮንትሮባንድ እቃዎች ተያዙ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ124 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመቱ የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዛቸውን የጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
የተያዙት የኮትሮባንድ እቃዎችም 101 ነጥብ 9 ሚሊየን የገቢ እና 22 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር የወጪ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
ከኮንትሮባንድ እቃዎቹ መካከል አልባሳት፣ ነዳጅ፣ የቁም እንስሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድኃኒት፣ ተሽከርካሪዎች፣ የመዋቢያ እቃዎች የጦር መሳሪያዎች፣ ጫት፣ አደንዛዥ እጾች፣የምግብ ዘይት እና የተለያዩ ሀገር ገንዘቦች ይገኙበታል፡፡
የገቢ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር ረገድ ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዙት ሀዋሳ፣ አዳማ እና ሞያሌ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ናቸው፡፡
የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በፍተሻ፣ በበረራና በጥቆማ መያዛቸውን የጉምሩክ ኮሚሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
የኮንትሮባንድ እቃዎቹን ሲያዘዋውሩ የተገኙ 18 ግለሰቦች እና ስድስት ተሽከርካሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል ተብሏል፡፡