ሜሱት ኦዚል ጫማ መስቀሉን አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ጀርመናዊው የአማካይ ስፍራ ተጫዋች ሜሱት ኦዚል በ34 አመቱ ከእግር ኳስ ዓለም ራሱን ማግለሉን አስታውቋል፡፡
በጀርመኖቹ ሻልከ 04 እና ዌርደር ብሬመን የተጫወተው ኦዚል በ2010 የደቡብ አፍሪካ የዓለም ዋንጫ ከጀርመን ብሄራዊ ቡድን ጋር ባሳየው ድንቅ ብቃት የስፔኑን ሀያል ክለብ ሪያል ማድሪድ መቀላቀል ችሏል፡፡
በሳንቲያጎ ቤርናባው ከሪያል ማድሪድ ጋር የላሊጋውን ዋንጫ ማሸነፍ የቻለ ሲሆን በፈረንጆቹ 2013 የክለቡ ክብረ ወሰን በሆነ ዋጋ የእንግሊዙን ክለብ አርሰናል ተቀላቅሏል፡፡
በአርሰናል ቆይታው በፈረንሳዊው አሰልጣኝ አርሰን ዌንገር ስር በክለቡ ድንቅ ብቃቱን ማሳየት ችሏል።
ከእርሳቸው ክለቡን መልቀቅ በኋላ በአሰልጣኝ ኡናይ ኢምሬ እና በተለይም ሚኬል አርቴታ የመሰለፍ እድል አለማግኘቱን ተከትሎ ከክለቡ ጋር ተለያይቶ ወደ ቱርክ በማቅናት የእግር ኳስ ህይወቱን ቀጥሏል።
በቱርክ ቆይታውም በፌኔርባቸ እና ኢስታንቡል ባሻክሼር ያልተሳካ ጊዜን አሳልፏል።
ኦዚል ከአርሰናል ጋር የኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫዎች ያነሳ ሲሆን፥ የ2014ቱን የዓለም ዋንጫም ከጀርመን ብሄራዊ ቡድን ጋር አሳክቷል።
ኦዚል ለቡድን ጓደኞቹ በሚያቀብላቸው ያለቀላቸው የጎል እድሎች በበርካቶች ዘንድ ይታወሳል።