95ኛው የኦስካር ሽልማት ሥነ-ሥርዓት ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) 95ኛው የኦስካር ሽልማት ሥነ-ሥርዓት በሎስአንጀለስ ካሊፎርኒያ ተካሂዷል፡፡
“ኤቭሪ ቲንግ ኤቭሪ ዌር ኦል አት ዋንስ” የተሰኘው የሣይንስ ፊክሽን ፊልም እና በጀርመንኛ ቋንቋ የቀረበው የጦርነት ታሪክ ያለው ፊልም “ኦል ኳይት ኦን ዘ ዌስተርን ፍሮንት”በታጩበት የተለያዩ ዘርፎች ሽልማቶቹን መጠቅለላቸው ተገልጿል፡፡
95ኛው ዓመታዊ የኦስካር ሽልማት መርሐ-ግብር ሎስአንጀለስ ካሊፎርኒያ በሚገኘው ዶልቢ ቲያትር የተካሄደ መሆኑን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
ዕለተ-ዕሁድ “ኤቭሪ ቲንግ ኤቭሪ ዌር ኦል አት ዋንስ” የተሰኘው የ”መልቲ ቨርስ” ዕሳቤ ላይ የሚያጠነጥነው የሣይንስ ፊክሽን ፊልም ገኖ የዋለበት እና በሰባት ዘርፎች የኦስካርን ሽልማት የጠቀለለበት ቀን ሆኖ መዋሉም ተነግሯል፡፡
የሣይንስ ፊክሽን ፊልሙ ÷ ምርጥ ምሥል፣ ምርጥ ዳይሬክተር፣ ምርጥ ኦሪጅናል ስክሪን ፕሌይ እና በሌሎች ተጨማሪ ሦስት የትወና ምድቦች የኦስካርን ሽልማት መጠቅለሉ ነው የተገለጸወ።
በ1929 የፀረ-ጦርነት ታሪክ ልብ-ወለድ መፅሐፍ ላይ ተመሥርቶ በጀርመንኛ ቋንቋ የተሠራው “ኦል ኳይት ኦን ዘ ዌስተርን ፍሮንት” የተሠኘው ፊልምም በአራት ዘርፎች የኦስካርን ሽልማትን አሸንፏል፡፡
የዘንድሮው የኦስካር ሽልማት የእስያ አርቲስቶችን በትወናው ዘርፍ በዕጩነት ማካተቱም በዘገባው ተመላክቷል፡፡
በትናንቱ ውሎ የ60 ዓመቷን ሚሼል ዮህ ከእስያ የመጀመሪያዋ ምርጥ ተዋናይት ተብላ የኦስካር አሸናፊ መሆኗም ታውቋል፡፡
ቬትናማዊው ኬ ሁይ ኳን ደግሞ “ኤቭሪ ቲንግ ኤቭሪ ዌር ኦል አት ዋንስ” ላይ ባሳየው ብቃት በምርጥ ረዳት ተዋናይ ዘርፍ ኦስካሩን አሸንፏል።
በተጨማሪ ሕንድ በምርጥ የፊልም ማጀቢያ ዘፈን ለመጀመሪያ ጊዜ እጩ ሆና ኦስካርን ማሸነፍ ችላለች፡፡