በአረንጓዴ ዓሻራ የሚተከሉ ችግኞች የፅድቀት ምጣኔያቸው እንዲጨምር በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተጠቆመ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአረንጓዴ ዓሻራ የሚተከሉ ችግኞች የፅድቀት ምጣኔያቸው እንዲጨምር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የአማራ እና የጋምቤላ ክልሎች ገለጹ።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክተር እስመለአለም ምህረት ÷ በክልሉ ባለፈው ዓመት በአረንጓዴ አሻራ ከተተከለው ከ1 ነጥብ 4 ቢሊየን በላይ ችግኝ ወደ 84 በመቶ የሚሆነው መፅደቁን ተናግረዋል።
በክልሉ ከ1 ነጥብ 5 ቢሊየን በላይ ችግኝ ለመትከል ዝግጅት መጀመሩን ጠቅሰው ÷ ከ400 ሚሊየን በላይ ችግኝም ዝግጁ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡
ለችግኝ መትከያ የሚሆን ከ176 ሺህ ሄክታር በላይ መሬትም እስካሁን መለየቱንም ነው ያነሱት፡፡
የጋምቤላ ክልል ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ቢሮ ሀላፊ አቶ አጃክ ኡቻን በበኩላቸው ÷ ባለፈው ዓመት በክልሉ ወደ 10 ሚሊየን የሚጠጋ ችግኝ መተከሉን ገልጸው ፥ ከ83 በመቶ በላይ የሚሆነው መፅደቁን ተናግረዋል፡፡
በክልሉ በዚህ ዓመት ከ10 ሚሊየን በላይ ችግኝ ለመትከል እንዲሁም ውጤታማ ስራዎችን ለመስራት የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓልም ብለዋል።
የክልሎቹ ግብርና ቢሮዎች ለፋናብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት ÷ የአረንጓዴ አሻራን ውጤታማ የሚያደርጉ ስራዎች ላይ ትኩረት ተደርጓል።
በዙፋን ካሳሁን