የዓድዋ ድል የቅኝ አልገዛም ባይነት፣ የባርነትና የጭቆና ጠል እንቅስቃሴ ውጤት ነው – አቶ አወል አርባ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓድዋ ድል የቅኝ አልገዛም ባይነት፣ የባርነት እና የጭቆና ጠል እንቅስቃሴ ውጤት ነው ሲሉ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ገለጹ፡፡
ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ÷ የ127ኛው የዓድዋ ድል በዓልን አስመልክቶ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልዕክታቸውም÷ለኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች የመላው ጥቁር ህዝቦች የአሸናፊነት ስነ ልቦና ተምሳሌት ለሆነው ለ127ኛው የዓድዋ ድል እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል፡፡
የዓድዋ ድል የአንድነት፣ የጅግንነትና የፅናት ተምሳሌት መሆኑን አውስተው÷አባቶች ሀገር ሊወር የመጣ ወራሪን ከጫፍ እስከ ጫፍ አንድነታቸውን አጠናክረው፣ ጀግንነትን አንግበው በፅናት በመፋለም ጠላት ያልጠበቀው ሽንፈት እንዲከናነብ ማድረግ ችለዋል ብለዋል፡፡
የእነሱ ድል ማድረግም በወቅቱ የተጠናቀቀ ድል ብቻ ሳይሆን ለትውልድ የሚተላለፍ ፣ለኢትዮጵያውያን፣ አፍሪካውያን ብሎም ለጥቁር ህዝቦችና ለመላው ለነፃነት ለሚታገሉ ህዝቦች ትልቅ አርአያ ሆኖ ሁሌም እየተገለጠ የሚጣቀስ ዋቢ መፅሀፍ እንዲሆን አድርገው አልፈዋል ነው ያሉት፡፡
የዓድዋ ድል ትልቁ ምስጢር የአባቶች የጠነከረ አንድነት ፣ ሀገርን ያስቀደመ በተግባር የሚገለፅ ጀግንነትና ዓላማን ዳር ለማድረስ የነበራቸው የበረታ ፅናት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ከምስራቅ፣ ከምዕራብ፣ ከደቡብ፣ ከሰሜን ‘ሀገሬን’ ብሎ የተሰባሰበው አርበኛ ለአንድ አላማ ሀገርን ከወራሪ እና ከቅኝ ግዛት የማዳን የፀና የሀገር ፍቅርን በማሳየት የህይወት መስዋዕትነት በመክፈል ሀገርን ከነሙሉ ክብሯ ለቀጣይ ትውልድ ማስተለለፍ ችሏል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የበለፀገች፣ የዜጎቿን የምግብ ዋስትና ያረጋገጠች፣ ሰላማቸው የተጠበቀ ህዝብ እንድንሆን ሁላችንም በየተሰማራንበት መስክ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ይጠበቅብናል ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
አባት አርበኞች ነፃነታችንን ማረጋገጥ እንደቻሉት፣ እኛ ደግሞ እውቀታችንን፣ ጊዜያችንን እና ጉልበታችንን በማቀናጀት ከድህነት ራሳችን ነፃ ማድረግ ይኖርብናል ብለዋል።
የአሁኑ ትውልድም የአባቶቹን ታሪክ በመድገም ለችግሮች ሀገር በቀል መፍትሄ መነሻ በማድረግ ችግሮችን በብልሃትና በጥበብ በመፍታት ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካ ብሎም ለዓለማችን ችግሮች ሁነኛ መፍትሄ ሆኖ ሊገኝ ይገባል ብለዋል፡፡
ለእድገትና ለሰላም ጉዞ ለሚያጋጥሙ መሰናክሎች እጅ ባለመስጠት፣ ተስፋ ለማስቆረጥ ለሚሞክሩ እንቅፋቶች ባለመገዛት ወደ ፊት የሚታየውን ብሩህ ተስፋና ልምላሜ አርቆ በመመልከት በጀግንነትና በፅናት በመጓዝ በርካታ መሰል የአድዋ ድሎችን እያመስዘገብን ወደ ተሻለ ከፍታ መሸጋገር እንችላለንም ነው ያሉት።