በጤና ተቋማት ያለው የመድሀኒት አቅርቦት 84 በመቶ ደርሷል ተባለ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት 6 ወራት በጤና ተቋማት በየደረጃቸው ያለው የመድሀኒት አቅርቦት 84 በመቶ መድረሱን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
ሚኒስቴሩ ባቀረበው የ2015 ዓ.ም የ6 ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት እንደገለጸው÷ ባለፉት 6 ወራት በግዥና በዓይነት በእርዳታ የተሰጡ 22 ቢሊየን 374 ሚሊየን 638 ሺህ 711 ነጥብ 22 ብር ዋጋ ያላቸው የጤና ግብዓቶች ወደ መጋዘን ገብተዋል።
በዚህ ወቅት 14 ነጥብ 9 ቢሊየን ዋጋ ያላቸው መድኃኒቶች፣ሪኤጀንቶች፣ የህክምና መገልገያዎችና መሳሪያዎች ለጤና ተቋማት ማሰራጨት መቻሉም በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡
ከዚህ ባለፈም 1 ነጥብ 98 ቢሊየን ብር ዋጋ ያላቸው የህክምና መሳሪያዎች ከማዕከል መጋዘኖች መሰራጨታቸውንም አስታውቋል፡፡
ለመድሃኒት ግዥ ይወስድ የነበረውን የቀን ብዛት ከ229 ወደ 160 ቀናት ለመቀነስ ታቅዶ በግማሽ ዓመቱ 202 ቀናት ማድረስ መቻሉም ነው የተገለጸው።
ከመድሀኒት ግዥ ጋር በተያያዘም በሥድሥት ወራቱ 9 ነጥብ 08 ቢሊየን ብር ከውጭ ሀገር እና 548 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር ከሀገር ውስጥ ግዥ መፈጸሙንም ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቀው፡፡