ከድጎማ ስርዓቱ አሠራር ውጭ በሆነ መንገድ በሚንቀሳቀሱ አሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከነዳጅ ድጎማ ስርዓቱ አሠራር ውጭ በሆነ መንገድ በሚንቀሳቀሱ አሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስቴሩ እንዳለው የነዳጅ ድጎማ ስርዓቱ ከሚፈቅደው አሠራር ውጭ በሆነ መንገድ ለመጠቀም የተተመነላቸውን የትራንስፖርት ታሪፍ የማያከብሩ፣ የስምሪት መስመራቸውን በአግባቡ የማይሸፍኑ አሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው፡፡
እንዲሁም ከስምሪት ውጪ በመሆን በኮንትራት ስራ ላይ በመሰማራት ተገቢውን አገልግሎት ለሕብረተሰቡ በማይሰጡ አሽከርካሪዎች ላይ አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝ ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ከሚመለከታቸው ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ተሽከርካሪዎችን ከድጎማ ተጠቃሚነት ምዝገባ እንዲታገዱ በደረሱ ሪፖርቶች መሰረት 3 ሺህ 140 ተሽከርካሪዎች ከአዲስ አበባ፣ ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ድሬደዋ፣ ጋምቤላ፣ ደቡብ ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልሎች እና በፌደራል ደረጃ በቀረቡ ሪፖርቶች መሰረት እንዲታገዱ ተደርጓል፡፡
በድጎማ ስርዓቱ መሰረት የሚጠበቅባቸውን አሟልተው ሲገኙና ተገቢው የህግ እርምጃ እንደተወሰደባቸው ሲረጋገጥ ዳግም ወደ ድጎማ ተጠቃሚነት እንዲመለሱ በማድረግ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛል ተብሏል፡፡
መንግስት የነዳጅ ዋጋ ድጎማን በሂደት በማስቀረት ወደ ቀደመው የዋጋ ማረጋጊያ ፈንድ አስተዳደር ሥርዓት ለመመለስ የሚያስችል የዋጋ ማስተካከያ እና የታለመ ነዳጅ ድጎማ ሥርዓት እንዲተገበር በወሰነው መሰረት ከሐምሌ ወር 2014 ዓ.ም ጀምሮ የብሔራዊ የታለመለት ነዳጅ ድጎማ ተግባራዊ መደረጉ ይታወሳል፡፡