Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ ባለፉት ሥድሥት ወራት በርካታ ውጤታማ ስራዎች ተከናውነዋል-ከንቲባ አዳነች

አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፉት ሥድሥት ወራት በርካታ ውጤታማ ስራዎችን ማከናወን እንደተቻለ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ፡፡

ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የካቢኔ አባላት የ2015 ዓ.ም የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት የስራ አፈፃፀም ግምገማ ተጠናቋል፡፡

ከንቲባ አዳነች በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷ባለፉት ሥድሥት ወራት በፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ እያለፍን በርካታ ውጤታማ ስራዎች ማከናወን የተቻለበት ፤ እቅዶቻችንን ለመፈፀም የታየው ትጋትና ተነሳሽነት አበረታችና ተስፋ ሰጪ መሆኑን ያየንበት ነበር ብለዋል፡፡

በተለይም የተቋም ማሻሻያ ስራ አገልግሎት አሰጣጡ ላይ ለውጥ የሚያመጣ ተስፋ ሰጪ ስራዎች መሰራታቸውን ብሎም የከተማዋን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴና የስራ እድል በመፍጠር ለውጥ የሚያመጡ ታላላቅ ፕሮጀክቶች በመልካም አፈፃፀም ላይ እንደሚገኙ ገምግመናል ነው ያሉት።

ይሁን እንጂ አሁንም የሕዝቡን ፍላጎትና ጥያቄዎች ለመቅረፍና የተጀመረው ፈጣን የለውጥ ጉዞ ለማስቀጠል ከእስካሁኑ በበለጠ ጉልበት አድሰን አንድነታችንን አጠናክረን ለላቀ ውጤት ልንተጋ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡

ሌብነትና ብልሹ አሰራርን በቁርጠኝነት በመታገል፣ተቋማዊ አቅም በማጠናከር፣የሪፎርም ስራዎችን በማከናወንና የመፈፀም አቅማችንን ከፍ በማድረግ ለህዝባችን የተሻለ እንዲሁም የዘመነ አገልግሎት ማቅረብ እንዳለብን አፅንኦት ሰጥተን ተመልክተናል ብለዋል፡፡

አዲስ አበባን አዲስና ውብ ብሎም ለነዋሪዎቿ የምትመች ፤ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ወገኖቻችንን በላቀ ሁኔታ የምትደግፍ ፤ መረዳዳትና መደጋገፍ የሰፈነባት እንድትሆን የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.