አቶ ደመቀ በውጭ ግንኙነት እንቅስቃሴ ለኢኮኖሚና ፖለቲካ ዲፕሎማሲ ትኩረት እንደሚሰጥ ገለጹ
አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በውጭ ግንኙነት እንቅስቃሴ ለኢኮኖሚ፣ ፖለቲካና የባህል ዲፕሎማሲ ትኩረት እንደሚደረግ ተናገሩ፡፡
አቶ ደመቀ ፥ በአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም ለሚሲዮን መሪዎች “የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ በተለወጠው የዓለም አሰላለፍ ” በሚል ማብራሪያ አቅርበዋል፡፡
በዚህም ለኢኮኖሚ ፣ፖለቲካ የባህልና የስፖርት ዲፕሎማሲ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራና የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ ቁልፍ ሀገራዊ ተቋሞችን ለስኬታማ የስራ ስምሪት አቀናጅቶ መጠቀም እንደሚገባ ተናግረዋል ።
የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ዓለማቀፋዊ ፈተናዎችን እንዲሻገር ከውስጣዊ ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት ጎረቤት ሀገራት ላይ በማተኮርና ለቀጠናው እና ለፓን አፍሪካ እሳቤ ልዩ ትኩረት በመስጠት በሁለትዮሽና በባለ ብዙ ወገን መድረኮች ላይ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም የማስጠበቅ ስራ በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡
የዲፕሎማሲ ስራን በተመሳሳይ መንገድ በመስራት የተለየ ለውጥ ማምጣት እንደማይቻል ያስታወሱት አቶ ደመቀ፥ ዲፕሎማቶች ሙያዊ ክህሎታቸውን በየወቅቱ በማሳደግ ፈተናዎችን በብቃትና በፅናት ለመሻገር ሁሌም ቀድመው እንዲዘጋጁ አሳስበዋል ።
ኢትዮጵያ ተመድን ጨምሮ የባለብዙ ወገን መድረኮችን በብቃት በመጠቀም የተጠናከረ ስራ እንደምትሰራም ነው አቶ ደመቀ የገለጹት፡፡
የዓለምን የውጭ ግንኙነት የፈተኑ ሁኔታዎችን በሚመለከትም ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ፥ ዲፕሎማቶች አነዚህ ሁነቶች ውስጥ የሚፈጠሩ የሀገራትን አካሄድና ፍላጎት በንቃት ተገንዝበው ለኢትዮጰያ ጠቃሚ የሆኑ ስራዎችን ማከናወን እንዳለባቸው ተናገረዋል።
የዲፕሎማሲ ድልን በመንግስት ተቋም ብቻ ማሳካት እንደማይቻል እና ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ማሳተፍ እንደሚገባ ወቅታዊውን የዓለም ሁኔታ በምሳሌነት በመጥቀስም ገለጻ አድርገዋል፡፡
በቀጣይ በሁሉም ሚሲዮኖች የተቀናጀ የዲጂታልና የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስራ መሰራት እንዳለበትም መጠቆማቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡