የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የአፍሪካ ጉብኝታቸውን በኢትዮጵያ ጀመሩ
አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቅርቡ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ቺን ጋንግ በስልጣን ዘመናቸው የመጀመሪያ የሆነውን ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ለማድረግ ዛሬ ኢትዮጵያ ገብተዋል።
ቺን ጋንግ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ÷ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እና ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።
በአምስት የአፍሪካ ሀገራት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት የሚያደርጉት የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር÷ ኢትዮጵያን የጉብኝታቸው መጀመሪያ አድርገዋል።
በኢትዮጵያ ቆይታቸውም የሁለቱን ሀገራት የጠበቀ ግንኙነት ወደ ላቀ ምዕራፍ ለማሳደግ የሚረዱ ውይይቶች ያደርጋሉ ተብሏል።
ቺን ጋንግ÷ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ ከአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማኸመት እና ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች ጋር እንደሚመክሩ ይጠበቃል።
በትዕግሥት አስማማው