36ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔን ለማስተናገድ ምክክር ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) 36ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ እና 41ኛውን የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ ከተለያዩ መሥሪያ ቤቶች የተወጣጣው ብሔራዊ ኮሚቴ ምክክር አድርጓል፡፡
በወቅቱም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ባለፈው ዓመት 35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ኮቪድ -19 ወረረሽኝ እና አገራችን በውጭ ጫናዎች ሥር ሆና ስኬታማ ጉባዔ ማስተናገዷን አስታውሰዋል።
ሚኒስትር ዴኤታዋ 36ኛው የመሪዎች ጉባዔ በተሻለ ሁኔታ እንዲካሄድ እያንዳንዱ ተቋም በቂ ዝግጅት ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
የተለያዩ ተቋማት ተወካዮቹም እ.ኤ.አ. ከየካቲት 15 እስከ 19 ቀን 2023 ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው ጉባዔ ላይ አገራችን ያለባትን ልዩ ኃላፊነት ታሳቢ በማድረግ የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት በትጋት እንደሚሰሩ መግለፃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መረጃ ያመለክታል።