የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የአሜሪካ ጉብኝት በኢትዮጵያና በዓለም አቀፍ ተቋማት መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያጠናክር ነው – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የአሜሪካ ጉብኝት በኢትዮጵያና በዓለም አቀፍ ተቋማት መካከል ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሚያጎለብት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም የኢትዮጵያን ወቅታዊ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ በተመለከተ ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
አምባሳደር መለስ ዓለም እንዳሉት÷ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የአሜሪካ ጉብኝትና የአሜሪካ አፍሪካ ስብሰባ ተሳትፎ የኢትዮጵያን ውጤታማ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ በጉልህ ያሳየ ነው።
ኢትዮጵያና አሜሪካ ያላቸውን የቆየ ወዳጅነት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የበለጠ የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸው፥ የአውሮፓ ህብረትና አሜሪካ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የሰላም ግንባታና መልሶ መቋቋም እንደሚደግፉ ተናግረዋል።
በዚህም የዓለም ባንክ ከድህረ ጦርነት በኋላ ለሰላምና መልሶ ግንባታ 745 ሚሊየን ዶላር የልማት ድጋፍ ለማድረግ መወሰኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ ባስመዘገበችው ስኬት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሽልማት እንደተበረከተላቸው አስታውሰው÷ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርም የመላ አፍሪካውያን የጋራ ፕሮጀክት እየሆነ ነው ብለዋል።
በተጨማሪም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በአዲስ አበባ ከሚኖሩ የአውሮፓ ህብረት ተወካዮችና አምባሳደሮች ጋር ፍሬያማ ውይይት እንዳደረጉ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።