ከ100 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የቀዶ ሕክምና ማዕከል ተመረቀ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ100 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የወላይታ ሶዶ ክርስቲያን ሆስፒታል የቀዶ ሕክምና ማዕከል ተመረቀ፡፡
የቀዶ ሕክምና ማዕከሉ ግንባታ 90 በመቶ የሚሆነው ወጪ በአሜሪካ ተራድዖ ድርጅት መሸፈኑ ተገልጿል፡፡
10 በመቶ የሚሆነው ወጪ ደግሞ በሆስፒታሉ አስተዳደር መሸፈን መቻሉን የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤፍሬም ገብረሥላሴ ተናግረዋል፡፡
የግንባታው መጠናቀቅ ከዚህ ቀደም ሲሰጥ የነበረውን አገልግሎት በ35 በመቶ ከፍ ያደርጋል ተብሏል።
ሆስፒታሉ ከ50 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ ለቀዶ ሕክምና ተማሪዎች የሚሆን የመኖሪያና የመማሪያ ኅንፃ ግንባታ በቀጣይ ለማካሄድም የመሰረተ ድንጋይ አስቀምጧል፡፡
ሆስፒታሉ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ከማገልገል አልፎ ከምስራቅ አፍሪካ ለሚመጡ ተገልጋዮች አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝም ተነግሯል፡፡
በታሪክነሽ ሴታ