የአምራች ኢንዱስትሪ ዕድገትን የሚያጠናክር ውይይት ከጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ ጋር ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአምራች ኢንዱስትሪ ዕድገትን የሚያጠናክር ውይይት ከጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) ጋር ተካሄደ፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀሰን ሙሃመድ የጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ የድህረ ምረቃ የፖሊሲ ጥናቶች ተቋም ፕሮፌሰር ኬኒቺ ኦህኖ የተመራ ልዑክ በቢሯቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ እና በጃፓን መንግስት መካከል ተከታታይ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ውይይት ሲደረግ እንደነበር ሚኒስትር ዴኤታው ጠቁመው በቀጣይም ውይይት ለማድረግ በዝግጅት ምዕራፍ ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
አያይዘውም በተለይም በእስያ ያለውን የአምራች ኢንዱስትሪ ምርታማነትና የቴክሎጂ አጠቃቀም፣ የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን፣ የጃፓንን ወርቃማ የአምራች ኢንዱስትሪ ተሞክሮ አጋርተዋል፡፡
በተጨማሪም በመንግስትና የአምራች ኢንዱስትሪ ባለቤቶችን አቅም ማሳደግና ውጤታማነት ልምድ ለመካፈል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
እንደ ሀገር የአምራች ኢንዱስትሪውን እድገት ለማሳለጥና ኢኮኖሚውን ለማሳደግ የግል ባለሀብቶች ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ያሉ መልካም ተሞክሮዎች በተለይም እንደ ሀገር የተጀመረውን የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለመደገፍ ፍቃደኛ መሆናቸውንም ነው የገለጹት፡፡
በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚታየውን የፖሊሲ አለመናበብ፥ ሰርቶ ማሳያ በማዘጋጀት ለማጠናከር በሁለቱም ወገኖች በኩል በርካታ ስራዎች እንደሚሰራ መናገራቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡