በአዲስ አበባ ከተማ ባሉ ክፍለ ከተሞች ከነዋሪዎች ጋር በወቅታዊ ከተማዊ ጉዳይ ላይ ውይይት ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ባሉ ክፍለ ከተሞች በዛሬው ዕለት ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ከተውጣጡ ነዋሪዎች ጋር በወቅታዊ ከተማዊ ጉዳይ ላይ ውይይት ተካሄደ።
የትምህርት ቤቶች ሰላማዊ መማር ማስተማር ላይ ትኩረቱን ባደረገው ውይይት የትምህርት ተቋማትን መጠበቅና የተጣለባቸውን ተልዕኮ እንዲወጡ ለማድረግ ህብረተሰቡ ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት ተገልጿል።
ትምህርት ቤቶች በትምህርት ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ማድረግ እንደሚገባና ተቋማቱንና ተማሪዎችን ለሌላ ተልዕኮ መጠቀሚያ የሚያደርጉ አካላትንም መከላከልና አሥፈላጊውን እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ በመድረኩ ተነስቷል።
በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ በውይይት መድረኩ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ የህዝብ ግንኙነት አማካሪ አቶ አለማየሁ እጅጉ፥ ሌላ የፖለቲካ አጀንዳ ያላቸው አካላት ሀገራዊ የልማትና ሠላም መሥፈንን ለማደናቀፍ በተለይም ትምህርት ቤቶችን መጠቀሚያ ለማድረግ መሞከራቸውን ገልጸዋል።
ይሁን እንጅ የከተማ አሥተዳደሩ ከነዋሪው ጋር በመሆን ችግር በሚፈጥሩ አካላት ላይ አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድና የሚወድም ንብረት የህዝብ በመሆኑ ማህበረሠቡ መጠበቅ እንደሚገባው አስገንዝበዋል።
የውይይቱ ተሣታፊዎችም ወላጆች ልጆቻቸውን ከመቆጣጠር ጀምሮ ተቋማቱን በመጠበቅና ችግር የሚፈጥሩ አካላትን በማጋለጥ ከመንግሥት ጋር በትብብር መሥራት ይገባል ማለታቸውን የከንቲባ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል።