ሶማሊያ አልሸባብን በማዳከም ረገድ የኢትዮጵያ ሠላም አስከባሪ ሃይል አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ገለጸች
አዲስ አበበ፣ ሕዳር 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አልሸባብን በማዳከም እና በማጥፋት ረገድ የኢትዮጵያ ሠላም አስከባሪ ሃይል አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ሲሉ የሶማሊያ ብሔራዊ ሠራዊት የ43ኛ ብርጌድ ዋና አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል አሊ መሃመድ ገለጹ፡፡
ጄኔራል አሊ መሀመድ ከኢትዮጵያ 7ኛ ሞተራይዝድ ሠላም አስከባሪ ሻለቃ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በወቅታዊ የፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል፡፡
ጄኔራሉ የኢትዮጵያ 7ኛ ሞተራይዝድ ሠላም አስከባሪ ሻለቃ የሠራዊት አባላት እና አመራሮች ለሶማሊያ ሠላም መስፈን እያደረጉት ላለው የሰላም ማስከበር ተልዕኮ አድናቆታቸውን መግለጻቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ መላክታል፡፡
አንድነታችንን በማጎልበት በኪስማዩ የተጀመረውን አልሸባብን የማዳከም እና የመደምሰስ ስራ አጠናክረን መቀጠል አለብን ነው ያሉት ዋና አዛዡ፡፡
የ7ኛ ሞተራይዝድ ሻለቃ ዋና አዛዥ ኮሎኔል ወዳጅ ቦጋለ በበኩላቸው÷ ከተሰጡን ተልዕኮዎች መካከል አንዱ እና ወሳኙ አሁን ያለውን የሶማሊያ መንግስት እና የፀጥታ ሃይሎችን ማጠናከር እና መደገፍ ነው፤ ይህንንም በጥሩ ውጤት እየሰራንበት ነው ብለዋል፡፡
አሸባሪው አልሸባብ የሶማሊያን ኢኮኖሚ እና ማህበራዊ የኑሮ ደረጃ ከመጉዳቱ ባሻገር የንፁሃን ዜጎችን ህይወት መቅጠፍ የዕለት ተዕለት ተግባሩ ነው ሲሉም ኮንነዋል፡፡