በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 100 ነጥብ 75 ኪሎ ግራም ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ መግባቱ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአንድ ወር ከ15 ቀን ብቻ 100 ነጥብ 75 ኪሎ ግራም ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ መግባቱን የክልሉ ማዕድን ቁጥጥር ግብረ-ኃይል አስታውቋል፡፡
የማዕድን ቁጥጥር ግብረ-ኃይሉ ከጥቅምት 1 እስከ ኅዳር 15 ቀን 2015 ዓ.ም ያለውን የሥራ አፈጻጸም ገምግሞ የቀጣይ አቅጣጫ አስቀምጧል።
የሚመረተው ወርቅ ሙሉ በሙሉ ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዳይገባ÷ ህገ-ወጥ የወርቅ ዝውውር ተፅእኖ እያሳደረ መሆኑን የተገለፀ ሲሆን ÷ ከሁለት ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ የታየው አፈፃፃም አበረታች መሆኑን አመላክቷል።
የወርቅ አምራቾችና አዘዋዋሪዎች ሕግን ተከትለው እንዲሠሩ ያሳሰበው ግብረ-ኃይሉ፣ ወደብሔራዊ ባንክ በማያስገቡ አምራቾች፣ አዘዋዋሪዎችና ሌሎች ተዋናዮች የጀመረውን ሕጋዊ እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ማስታወቁን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።