ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ያላቸውን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ተስማሙ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከሶማሊያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሳለህ አሕመድ ጋር በኒጀር ኒያሚ ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ያላቸውን የሁለትዮሽ እና ዘርፈ ብዙ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ተስማምተዋል፡፡
ሀገራቱ በተቻለ ፍጥነት የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባ ለማካሄድ መስማማታቸውንም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
አቶ ደመቀ መኮንን ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ያሏትን የተሻሉ ተሞክሮዎች ለሶማሊያ ለማካፈል ቁርጠኛ መሆኗን ተናግረዋል፡፡
የሶማሊያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሳለህ አሕመድ ጃማ በበኩላቸው ÷ የኢትዮጵያ ሰላም በሶማሊያም ሆነ አካባቢው ዘርፈ ብዙ ተፅእኖ እንዳለው አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትን በመከላከል ረገድ የሚደነቅ ስራ እያከናወነች እንደምትገኝም አውስተዋል፡፡