ለግብርናው የተሰጠው ትኩረት የምርት ጥራት ላይ ውጤት ማምጣቱ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ለግብርናው ዘርፍ የተሰጠው ልዩ ትኩረት በውጭ ገበያ የምርት ጥራትና አቅርቦት ውጤት ማምጣቱን የኢትዮጵያ ጥራጥሬና ቅባት እህሎች ላኪዎች ማኅበር ገለጸ፡፡
የማኅበሩ የቦርድ ሰብሳቢ ሲሳይ አስማረ እንደገለጹት÷ የዘርፉ ዳግም መነቃቃት ለላኪዎች ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሯል።
የግብርና ምርቶችን እሴት ጨምረው የሚልኩ ኢንዱስትሪዎች ለውጭ ምንዛሬ ግኝት አስተዋጽኦ እያደረጉ
መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ማኅበሩ 230 ሺህ ሜትሪክ ቶን ሰሊጥ ወደ ውጪ ለመላክ መዘጋጀቱን ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡
ለአርሶ አደሮች ከማሳ ጀምሮ አጠቃላይ የምርት ሂደት ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በዱባይ ዓለም አቀፍ የቅባት እህሎች ኮንፌዴሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ሬንዲ ዳኩሬት ኢትዮጵያ ለግብርናው ዘርፍ በሰጠችው ልዩ ትኩረት ጥራት ያላቸው ምርቶች ለዓለም ገበያ እየቀረቡ ነው ብለዋል፡፡